ቀጥታ፡

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚከናወኑ ስራዎችን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ መዘጋጁቱን አስታወቀ

ነቀምቴ ፤ ሰኔ 05/2013 ( ኢዜአ) ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል የሚከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ዘለቂ ለማድረግ በጥናትና ምርምር ለመደገፍ መዘጋጁቱን አስታወቀ ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከምዕራብ ሸዋ፣ ምሥራቅ፣  ምዕራብና  ቄለም ወለጋ እንዲሁም ቡኖ በደሌ ዞኖች ከተውጣጡ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በነቀምቴ ከተማ አውደ ጥናት አካሄዷል።

በአውደ ጥናቱ መድረክ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ ባቀቡት ጥናታዊ ጽሁፍ  በሀገሪቱን የአረንጓዴ አሻራ ልማት   የሚካሄደውን  የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርን በጥናትና ምርምር ተቋሙ ይደግፋል፡፡

በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅና አካባቢውን አረንጓዴ ለማልበስ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የህዳሴው ግድብ በደለል እንዳይሞላ ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስድሳ በመቶ የሚሆን የአባይ ገባር ወንዞች የሚመነጩት ከምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍሎች ነው ያሉት ዶክተር ሀሰን ወንዞቹ በደለል ተሞልተው በህዳሴው ግድብ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ በአካባቢው የተጠናከረ የደን፣ የአፈርና ፣ውሃ ጥበቃ ሥራው ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት አለበት ብለዋል።

ሀገሪቱ ከህዳሴው ግድብ  የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከሕዝቡ ጋር በመሆን ስራውን በጥናትና ምርምር በመደገፍ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የዓመቱን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እውን ለማድረግ እንዲያግዝ  1ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞች አዘጋጅቶ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ ትናንት መትከል መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ከአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል ነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ዶክተር ዓለምፀሐይ ተስፋ በሰጡት አስተያየት፤ ደን ሕይወትና አስትንፋስ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢን ጥበቃን በማስመልከት ያዘጋጀው መድረክ የሀገሪቱ አረንጓዴ ልማት ፕሮግራም ለማሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ከደለል ለመጠበቅ የደን፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች በማጠናከር ገባር ወንዞቹ ለዓባይ ንጹህ ውሃ እንዲገብሩ የአካባቢው ሕዝብ መረባረብ አለበት ብለዋል፡፡

በልጅነት የቀሰምነው እውቀት ከኛጋር ይቆያል ያሉት ዶክተር ዓለም ፀሐይ፤ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ህጻናትን ከልጅነታቸው ጀምሮ  ስለ ደን፣ አፈርና ውሃ አጠባበቅ ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው  ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ደረጀ ኢናሁ በበኩላቸው፤ የአባይ ተፋሰስን ለመጠበቅ ባለድርሻ አካላት   የውሃ ፍሰቱ እንዳይቀንስና የህዳሴው ግድብ በደለል እንዳይሞላ የአካባቢ ጥበቃ ስራን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተሻለ እርጥበታማ ቦታ ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ መሆኑን የተናገሩት  ዶክተር ደረጀ ፤ ለ50 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ሰፋፊ የመንግሥት እርሻዎች አሁንም በግል  ኢንቨስትመንት የቀጠለ  በመሆኑ አካባቢው እንዳይጎዳ በአግባቡ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

መንግሥትና ሕዝቡ በመተባበር በተፋሰሱ አካባቢ የሚያካሄዱትን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በተጠና መንገድ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም