ህብረተሰቡ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያለውን ግንዛቤ 99 በመቶ ማድረስ ተችሏል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያለውን ግንዛቤ 99 በመቶ ማድረስ ተችሏል ተባለ
ሰኔ 4፤2013 (ኢዜአ) ባለፉት 15 ወራት ህብረተሰቡ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያለውን ግንዛቤ 99 በመቶ ማድረስ መቻሉ ተገለጸ።
በህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት፣ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ጉባኤው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አገር ውስጥ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 15 ወራት በአገር አቀፋ ደረጃ ወረርሽኙን ለመከላከል በተሰሩ ስራዎች እና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ የተሰሩ የጥናት ውጤቶች ይፋ ተደርገዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ጊዜያት ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ በተሰሩ ስራዎች ወረርሽኙ ያደርስ የነበረውን የከፋ ጉዳት ለመቀነስ ተችሏል።
ማህበረሰቡ በወረርሽኙ ዙሪያ በከተማም ሆነ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍሎች ያለውን የማህበረሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በተሰሩ ንቅናቄዎችም ግንዛቤ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በጥናቱ መሰረትም ማህበረሰቡ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዙሪያ ያለውን የግንዛቤ ደረጃ 99 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከዚህም 54 በመቶ የሚሆነውን መረጃ ከሬድዮ፣ 47 በመቶ ከቴሌቪዥን፣ 20 በመቶ ከማህበራዊ ሚዲያዎች አንዲሁም አምስት በመቶ የሚሆነውን መረጃ ደግሞ ከኃይማኖት ተቋማት እና አባቶች በኩል ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።
ጥናቱ ህክምና አገልግሎት ከመስጠት፣ የላብራቶሪ አቅንም ከመገንባትና የቅኝት ዳሰሳ ስራዎችን በማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ገልጸዋል።
ወረርሽኙ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና የህዝቡን የእለተ እለት እንቅስቃሴ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የጥንቃቄ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ያመላከተ እንደሆነም ተናግረዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል በምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዙሪያ የጎላ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
ክትባቶች ብቁነታቸውንና ሌሎች ተዛማች ጉዳዮችን የመመርመርና ፍተሻ የማድረግ ሥራ ሲሰራ መቆየቱንም አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ከመከላከል ስራው ጎን ለጎን አዳዲስ የሚሰሯቸው የፈጠራ ስራዎችም ወደ ገበያው እንዲወጡና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ የስራ እድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከ273 ሺህ የሚልቁት ደግሞ ቫይረሱ የተገኘባቸው ናቸው።
1 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት የተከተቡ መሆናቸው ተገልጿል።
ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የወረርሽኙ መከላከል ሂደትና ችግር ፈቺ ምርምሮች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ ተመራማሪዎች በኩል ጥናቶች ቀርበው ውይይት የሚካሄድባቸው ይሆናል።