ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አረፉ። - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አረፉ።

ሰኔ 4፤2013 (ኢዜአ) ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አረፉ።
ከጥንታዊ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ጥናት መምህራን መካከል ግንባር ቀደም ይሰኛሉ ታላቁ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፡፡
በኢትዮጵያ የግእዝ ስነ-ጽሑፍ ታሪክ ወርቃማው ዘመን በሚሰኘው የመካከለኛው ዘመን ስነ- ጽሑፍን በጥልቀት አጥንተዋል።
ለሺህ ዓመታት የኢትዮጵያ ነገስታት የሥራ ቋንቋ በነበረውና ከአፍ መፍቻ ቋንቋነት ከወጣው ግእዝ የተራቀቁት ጌታቸው ኃይሌ 'አንድ አፍታ ላውጋችሁ' በተሰኘው ግለ-ታሪካቸው እንደሚያወጉት በአማርኛ፣ በግዕዝ፣ በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ፣ በጀርመንኛ፣ ወዘተ ቋንቋዎች የላቀ ችሎታ ነበራቸው።
በሰሜን ሸዋ ምንጃርና ሸንኮራ የተወለዱት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በልጅነታቸው በአብነት ትምህርት አዕምሯቸውን አስልተዋል።
በዘመናዊ ትምህርት ቤት ቀጥለውም ለከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ወደ ግብጽ ካይሮ አቅንተዋል።
በካይሮ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ከኮፕቲክ ስነ-መለኮት ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1957 ተከታትለዋል።
የሦስተኛ ዲግሪያቸውንም በ1962 ከጀርመኑ ቱቢግን ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል። ሌሎች ተጨማሪ ትምህርቶችንም በእሥራኤልና በአሜሪካ ተከታትለዋል።
በቤተ-ክህነትም በዓለማዊው ዕውቀትም የበቁት ፕሮፌሰር ጌታቸው ከ1950 እስከ 1960ዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሴማዊ ቋንቋ ጥናት፣ በአማርኛ ግዕዝ ስነ-ጹሑፍ እና ሰዋሰው በመምህርነት አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ አብዮት ከፈነዳበት ከ1966 በኋላ በደርግ ሥርዓት በደረሰባቸው ግፍ ለአካላዊ ጉዳት ተዳርገዋል።
አካላዊ ጉዳት ቢደርስባቸው ቅሉ ታላቁ ሊቅ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ የኢትዮጵያን ጥንታዊ መዛግብት አገላብጠዋል፤ መርምረዋል፤ ሰንደው ለትውልድ ቅርስ አስቀምጠዋል።
በአውሮፓውያኑ ዘመን ቀመር በ1976 ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ተሰደዋል።
በኋላም በአሜሪካ ሚኒሶታ በሚገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እስከ ማምሻ እድሜያቸው በፕሮፌሰርነት አገልግለዋል። ዩኒቨርሲቲውም ከፍተኛውን የአስተማሪነት ማዕረግ (ሪጀንት ፕሮፌሰር) ሰጥቷቸዋል።
በቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ ከአምስት ሺህ በላይ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትን ለጥናትና ምርምር አከማችተዋል፤ ከእነዚህም መካከል 10 ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትን በማይክሮ ፊልም እንዲቀረጹ አስችለዋል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የዓለም ሊቃውንትን እየመረጠ በየዓመቱ በሚመዘግበው የእንግሊዙ የብሪቲሽ አካዳሚ ኢትዮጵያን ያስጠሩ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ምሑርም አባል ናቸው።
ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ጌታቸው ኃይሌ በ1980 ዓ.ም በአሜሪካ ሊቃውንት በሚሸለሙበት የማክአርተር ፋውንዴሽን ሽልማት አሸንፈዋል።
በዓለም አቀፍ ሊቃውንትንና የምርምር ተቋማት ዘንድ በጥልቅ ምርምራቸው አንቱ የተባሉ፣ የኢትዮጵያ ኩራት ሊቅ ነበሩ።
በተለይም በሴሚቲክ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ጥናት ወደር አልባው ምሑር እስኪሰኙ አንቱታን አትርፈዋል። ከ80 ያላነሱ የምርምር ሥራዎቻቸውን በእውቅ ዓለም አቀፍ ጥናታዊ መጽሔቶች አሳትመዋል።
በርካታ ጥንታዊ የግእዝ መጽሐፍትን ወደ አማርኛው መልሰዋል። ለአብነትም “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች”፣ “ደቂቀ እስጢፋኖስ”፣ “በህግ አምላክ”፣ “ባህረ ሐሳብ፣…” በሚል ርዕስ የተዘጋጁት ሥራዎቻቸው ሕያው ምስክር ናቸው። የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከደቂቅነት እስከ ልሂቅነት ልደት፣ ዕድገት፣ የትምህርት ሁኔታ፣ የቤተሰብ፣ የኃይማኖት፣ የሥራ፣ የጤናና የፖለቲካ ውጣ ውረድ ሕይወታቸውን የሚዘክረው 'አንድ አፍታ ላውጋችሁ' መጽሐፋቸው በምሑራን ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ አድርጓቸዋል።
ግለ-ታሪካቸው ላይ እንደተቀመጠውም በልጅነታቸው ጀምሮ ያሳለፉት ውጣ-ውረድ ሳይደብቁ አብጠርጥረው በውብ ቋንቋ ስለማስቀመጣቸው ሃያሲያን ይገልጻሉ።
በአብዮቱ ዘመን ካጋጠማቸው አደጋ በተዓምር ተርፈው ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ ውለዋል። በኢትዮጵያ ጉዳይ እስከ ዕለተ ሞታቸው በትጋት በመከታተል የሞገቱት አንጋፋው ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባደረባቸው ህመም ሲረዱ ቆይተው በዛሬው ዕለት በኒዮርክ ከተማ በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በታሪክ፣ የቋንቋና የስነ- ጽሑፍ ምርምሮች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ፣ የፍትሕ፣ የነፃነት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና በሀገራዊ ጉዳዮች በሳል ሐሳብ አመንጪና ሃያሲም ነበሩ።
ኢትዮጵያም ዛሬ የታሪኳን ፈልፋይ፣ የብራና ቅርሶቿ ዘብ፣ የጥንታዊ ስነ-ጽሑፍና ቋንቋዋ ጠበብቷን፣ የማንነቷን ገላጭና የጽሑፎቿን አሳሽ፣ ተርጓሚና መርማሪዋን፣ ብርቅዬ ባለውለታ ልጇን በሞት ተነጥቃለች። በርካታ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም በፕሮፌሰሩ ሕልፈት የተሰማቸውን ሐዘን እየገለጹ ነው።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከባለቤታቸው ምሥራቅ አማረ ያፈሯቸው አራት ልጆችና በጉዲፈቻ ያሳደጓቸው ሁለት ልጆች በድምሩ የስድስት ልጆች አባት ነበሩ።