የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ ያለንን አንድነት በተግባር ማሳየት አለብን- የተማሪዎች ህብረት - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ ያለንን አንድነት በተግባር ማሳየት አለብን- የተማሪዎች ህብረት
ጅማ፤ ሰኔ 04/2013 (ኢዜአ) ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ፈጥነን በማጠናቀቅ ያለንን ሀገራዊ አንድነት በተግባር ማሳየት አለብን ሲል የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ገለጸ።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት አባላት በሀገራዊ ጉዳይ በተካሄደው የቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ በመሳተፍ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
"ድምጻች ለነጻነታችንና ለሉአላዊነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ሙደስር ነጋ ፤ የሀገር ጉዳይ ከምንም በላይ በመሆኑ እኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተጠናቆ መመኪያችን እንዲሆን የጸና አቋም አለን ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በፍጥነት በማጠናቀቅ ያለውን ሀገራዊ አንድነት በተግባር ማሳየት እንደሚገባ ተናግሯል።
ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን አጠናክረው ለሀገራቸው ሉአላዊነት መከበር አቋማቸውን ለአለም ማሳየት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡
ሌላው የኮንፍረንሱ ተሳታፊ ተማሪ ያሲን አብደላ በበኩሉ ፤ ማንኛውም የውጭ ጫና እኛ ኢትዮጵያውያን የጸና አቋማችንን በማሳወቅ ግድቡ የነጻነታችን ምልክትና የሉአላዊነታችን መሰረት እንደሆነ ለሁሉም እናሳውቃለን ብሏል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ሀብት የመጠቀም መብታቸው ማንም ሊከለክላቸው እንደማይችል ለሁሉም ማሳወቅ እንደሚያስፈል ተናግሯል፡፡
ተማሪ መሰሉ ጥላሁን በሰጠችው አስተያየት፤ እራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ጉዞ ለማደናቀፍ የሚሞክር ማንኛውም አካል ደጋግሞ ማሰብ ይገባቸዋል ብላለች፡፡
ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ተባብረን በመስራት ጠላትን ልናሳፍር ይገባል ስትልም መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አመለወርቅ ህዝቅኤል በበኩላቸው፤ መርሀግብሩን ያዘጋጀው የተማሪዎች ህብረት መሆኑን ጠቅሰው ፤ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ድምጻቸውን ለማሰማት ፍላጎት ስለነበራቸው ነው ብለዋል፡፡
በቪዲዮ ኮንፈረንስ ከ40 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ህብረት አባላት በመሳተፍ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በመወያየት አቋማቸውን ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎቹ ሀገርን የሚረከቡና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በቅርበት የሚከታተሉ በመሆኑ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም ማሳየታቸው ተገቢ ነው ሲሉ ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል፡፡
የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች አንድነቷ የተጠበቀ ነጻና ሉአላዊት ሀገራቸው በማንኛውም አካል ተጽዕኖ ስር እንድትወድቅ እንደማይፈልጉ የታየበት ኮንፍረንስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡