ቀጥታ፡

ቻይና 400 ሺህ ዶላር ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶች ለኢትዮጵያ አበረከተች

ሰኔ 4/2013 ( ኢዜአ) የቻይና መንግሥት የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅን ለማሻሻል የሚረዳ 400 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁሶች ለኢትዮጵያ በድጋፍ አበረከተች።

የህክምና መሳሪያዎቹ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የንግድና ኢኮኖሚ ትብብር አማካሪ ሚስተር ያንግ ይሃንግ ለጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስስ አደል ኮደር አስረክበዋል።

ድጋፉ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ እያከናወነ ያለውን የእናቶች፣ የህጻናትና የጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅ ሞት ቅነሳ ላይ  የጀመረውን የአንድ ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት የሚያግዝ ነው ተብሏል።

ሚስተር ያንግ ድጋፉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸውን የረጅም ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተከትሎ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።

ከዚህም መካከል በጤና ዘርፍ ላይ ሙያተኛን ማብቃት፣ የጤና ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ማዘመንና የግብአት አቅርቦትን ማሟላት ተጠቃሽ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጤና ዘርፉ እያሳየችው ያለው የነቃ ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አማካሪው ለዚህም አስፈላጊ እገዛዎችን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅና የሞት ምጣኔን ለመቀነስ እያደረገች ያለው ጥረት ሊቀጥል የሚገባው በመሆኑ የቻይና መንግሥት 400 ሺህ ዶላር ወጪ የተደረገባቸውን የህክምና ቁሳቁሶችን አበርክቷል።

ድጋፉ በደቡብ እና በትግራይ ክልል በዩኒሴፍ የሚተገበረው የጤና ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮጀክትን የሚያግዝና በክልሎቹ ለተመረጡ የጤና ተቋማት ተደራሽ እንዲሆን ታልሞ የተበረከተ መሆኑንም አንስተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ፤ እንደ አገር የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻልና ለውጥ ለማምጣት እየተከናወነ ባለው ሥራ ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል ይላሉ።

በተለይም የእናቶች፣ የህጻናትና የጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅ ማሻሻልና ሞት ቅነሳ ላይ አበረታች ሥራ ቢከናወንም በጨቅላ ህጻናት ላይ ግን የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም ብለዋል።

በዚህም በቀጣይ አምስት ዓመት እቅድ ውስጥ ይህን በማሻሻል በአገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

ድጋፉ በክልሎቹ እየተስተዋለ ያለውን የግብአት እጥረት በማቃለልና የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅን በማሻሻል ረገድ አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆን አብራርተዋል።

ከአጋር አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከርና ለሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት በር የሚከፍት በመሆምኑ ይህን መሰሉን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስስ አደል ኮደር እንዲሁ በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍ የሚያስችል የአንድ ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የጤና ሥርዓታቸው ያልዘመነባቸውን አካባቢዎች በመለየት የተሻለ ቴክኖሎጂን ማስጀመርና የግብአት አቅርቦቶችን ማሟላትን ያካትታል።

በተለያዩ የጤና ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ሙያተኞችን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ዘመኑ የደረሰበትን የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠትንም እንዲሁ።

በዚህም የቻይና መንግሥት ያደረገው ድጋፍ ፕሮጀክቱን የሚያግዝና በተለይም በክልሎቹ በተመረጡት ዞኖች ላሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የእናቶች የወሊድ አገልግሎት እንዲሁም የህጻናትና የጨቅላ ህጻናት ህክምና በተሟላ መልኩ እንዲሰጥና ጥራቱ እንዲሻሻል የሚረዳ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም