በምርጫው ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሁሉም ለሰላምና አንድነት ዘብ መቆም እንዳለበት ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሁሉም ለሰላምና አንድነት ዘብ መቆም እንዳለበት ምሁራን ተናገሩ
ደሴ ፤ ሰኔ 4/2013(ኢዜአ) በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ አካሄደን ተከትሎ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ሁሉም ለሰላምና አንድነት ዘብ መቆም እንዳለበት በወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ፡፡
"ለሰላማዊ ምርጫ የዜጎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ጥናታዊ ጹሑፍ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የሰላም፤ ዲሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልዩ ውዱ እንደገለጹት፤ ምርጫ ዜጎች የሚፈልጉትን መሪ የሚመርጡበት የስልጣኔ መገለጫ አንዱ መንገድ ነው፡፡
ሆኖም ምርጫውን ምክንያት አድርገው የግል ጥቅማቸውን ለማካበት ሌት ተቀን የሚባክኑ የሴራ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ስድስትኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ አሸናፊ እንድትሆን ሁሉም ለሰላምና ለአንድነት ዘብ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሀገርና ህዝብ ሲሉ ተቀራርበው በመስራት ምርጫው የዴሞክራሲ መሰረት ጥሎ እንዲያልፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በተካሄዱ የውሸት ምርጫዎች ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ግርግርና ሁከት ንጹሃን ዜጎች መጎዳታቸውን ያስታወሱት ዶክተር አልዩ፤ ሁሉም ፓርቲዎች መሸነፍና ማሸነፍ የተፈጥሮ ህግ መሆኑን አውቀው ውጤቱን በፀጋ ለመቀበል ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ሌላው "የምርጫ ነክ ግጭቶች መንስኤ፣ ባህሪ፤ ተዋናይና ውጤቱ" በሚል ጹሑፍ ጹህፍ ያቀረቡት አቶ አያሌው ይመር በበኩላቸው፤ ውስጣዊና መዋቅራዊ የአሰራር ችግር፣ አግላይ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አለመረጋጋትና ግለሰብ ላይ የተንጠለጠለ ተቋም መኖር ለምርጫ ሁከትና ግጭት ምክንያት ይሆናሉ ብለዋል።
ጥንቃቄ ካልተደረገ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ሴረኞች፣ ፓርቲዎች፣ የፀጥታ መዋቅሩና ወገንተኛ መገናኛ ብዙሃን የግርግር ተዋናይ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
''ውጤቱ ደግሞ ከሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ባለፈ ሞት፣ የአካል ጉዳትና ንብረት ውድመት ነው'' ያሉት አቶ አያሌው፤ከዚህ የሚያተርፍ ስለማይኖረ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም ከወዲሁ በትብብር መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ታማኒነትና ፍትሃ ሆኖ እንዲፈጸም መንግስት የሰጠው ትኩረትና ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ "የምርጫውን የስነ ምግባር ደንብና መመሪያ ማስተግበር ለምርጫው ውጤታማነት ያለው ሚና" በሚል ጹሑፍ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ሰለሞን ጎራው ናቸው፡፡
አፋኝና ጨቋኝ ህጎች ተሻሽለው በአሳታፊ፣ ገለልተኛና የዲሞክራሲ መሰረት መጣል የሚያስችሉ ህግና ደንቦች መውጣታቸውን ጠቁመው ተግባራዊ ከሆኑ ምርጫውን ሰላማዊ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
ከህግና ደንቡ ውጭ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ፓርቲና ግለሰብ ተጠያቂ በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የዘንድሮ ምርጫ በሰላም ተጠናቆ ኢትዮጵያ አሸናፊ እንድትሆን መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የየድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በህዝብ ትግል የመጡ ለውጦች ዳር ሳይደርሱ ተጨናግፈው ቀርተዋል ብለዋል።
በተለይ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ተስፋ ሰጪ እድሎች ቢገጥሙንም በአጠቃቀምና ቅንጅት ክፍተት መጠቀምና ማዝለቅ እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
አሁንም በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የመጣው ለውጥ በጥቅመኞች እንዳይቀለበስ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል፤ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ መጠቀም ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ምርጫውን በሁሉም መለኪያዎች ውጤታማ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ አሸናፊ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ኢትዮጵያ ወርቅነህ በሰጡት አስተያት፤ ምርጫ በመጣ ቁጥር ህብረተሰቡ ከሚገጥመው ጭንቀትና ስጋት ነጻ እንዲሆን ዴሞክራሲው መጎልበት እንዳለበት ተናግረዋል።
በግጭት ጊዜ ሴቶችና ህጻናት ቅድሚያ ተጠቂ በመሆናቸው ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማገዝ በአካባቢያቸው ተደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎችም መሳተፋቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል፡፡