ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

መቀሌ፤ሰኔ 4/2013(ኢዜአ) በመቀሌ ከተማ በአዲሱ መንደራቸው የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ተዘርግቶ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን በመጀመራቸው መደሰታቸውን አስተያየት የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት በጀመረባቸው መንደሮች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሃፍተ ኪሮስ በሰጡት አስተያየት፤ ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ጥያቄ አሁን ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሚኖሩበት መንደር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን በመጀመራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሶስት ተማሪ ልጆቻቸው በኩራዝ መብራት እየተጠቀሙ የጤና ችግር ይደርስባቸው እንደነበር ያስታወሱት ሌላዋ የአካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ደመቀች አማረ፤ "ያሳለፍነው የጨለማ ጊዜ አብቅቶ ዛሬ የኤሌክትሪክ መብራት ተጠቃሚ በመሆናችን በጣም ተደስቻለሁ" ብለዋል።

በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ይግዛው ሐጎስ እንዳስታወቁት፤ በከተማዋ በሰባት አዳዲስ መንደሮች ሲካሄድ የነበረ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመር ዝርጋታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው በ2012 ዓ.ም በ19 አዳዲስ የከተማው መንደሮች እንደተጀመረ ጠቅሰው፤ አገልግሎት የጀመሩትም ከእነዚህ መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላላ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 25 ሺህ አባወራዎች ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ኢንጅነር ይግዛው፣ ጊዚያዊ አስተዳደሩ በመደበው በጀት የቀሩትን ለማጠናቀቅ ስራው መቀጠሉን ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ያገኙት መንደሮች የመስመር ዝርጋታ ደረጃውን የጠበቀና ስራው ለተቀሩትም መንደሮች የሃይል አቅርቦት ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ገብረ መድህን ናቸው።

በመቀሌ በሚገኙ 19 መንደሮች የመስመር ዝርጋታውን ለማጠናቀቅ 405 ሚሊዮን በጀት መያዙን አቶ መስፍን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም