ቦርዱ ሰኔ 14 ምርጫ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ቦርዱ ሰኔ 14 ምርጫ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች ይፋ አደረገ
ሰኔ 3/2013 (ኢዜአ) በተለያዩ ምክንያቶች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ በማይካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች ሁለተኛ ዙር ሀገራዊ ምርጫ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ያልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች መኖራቸውን ሲገልፅ መቆየቱን ቦርዱ አስታውሷል፡፡
በተጨማም ከመራጮች የድምፅ መስጫ ወረቀት ህትመት ጋር በተያያዘ ባጋጠመ ችግር በ32 ተጨማሪ የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ እንደማይካሄድ ቦርዱ ጠቁሟል፡፡
በመሆኑም በሶማሌ ክልል የሚገኙ ሁሉንም የምርጫ ክልሎች ጨምሮ ችግር ባጋጠመባቸው የምርጫ ክልሎች ሁለተኛ ዙር ሀገራዊ ምርጫ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ችግር ባላጋጠመባቸው ሌሎች የምርጫ ክልሎች ግን ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔም በሁለተኛው ዙር የሚካሄድ መሆኑን ሰብሳቢዋ ጨምረው ገልፀዋል።(ኢቢሲ)