ቀጥታ፡

አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሳካ በምርምር በመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ

አርባ ምንጭ ሰኔ 03/2013 (ኢዜአ) አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሳካ በዘርፉ የሰው ሃይል እያፈራና ምርምር እያደረገ በመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።
የዩኒቨርሲቲው  ተማሪዎች "ድምፃችን ለነፃነታችንና ሉዐላዊነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል።

በውይይት መድረኩ የዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገር ሉዐላዊነትና ነፃነት ላይ የማይናወጥ አቋም በማራመድ ከሌላው ይለያል።

ይህንን በመሸርሸር የህዳሴው  ግድብንና ምርጫውን ለማደናቀፍ ግብፅና ሱዳንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በሀገራችን ላይ እየፈጸሙ ነው ብለዋል።

የነሱን አፍራሽ እንቅስቃሴ ለማክሸፍና የህዝብን ጥቅም አሳልፎ ላለመስጠት በዲፕሎማሲውናድርድሩ ረገድ መንግስት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተገቢና ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።

ከሀገራችን የሚመነጭ ወንዝ እንዳንጠቀም የሚከለክለን ሕግ የለም ያሉት አቶ በድሩ፤ የኢትዮጵያ እናቶች ለኃይል ፍለጋ ዛሬም ከጭስ አለመላቀቃቸው ቁጭት የሚፈጥር እንጂ በተፅዕኖ ወደ ኋላ እንደማይመልሰው ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሳካ  በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚታወቀው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ምሁራንን ከማፍራት ባለፈ በግድቡ ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ የበከሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በግድቡ ዙሪያ ሀገራዊ አውደ ጥናቶችን በማስተናገድም እንዲሁ።

በተለይ ባለፉት ጊዜያት ፀረ-ሰላም ሃይሎች  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን እንደመሣሪያ በመጠቀም አሉታዊ አሻራ ለማሳረፍ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ይሀ ሁኔታ ተቀይሮ ተማሪው ካለማንም ጎትጓችነት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ያገባኛል በማለት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋልል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና አምስተኛ  ዓመት ተማሪ በረከት ብዙአየው በበኩሉ፤ ከጥንት ታሪካችን እንደምንረዳው የሀገራችን ሉዐላዊነት ለመድፈር የሚነሱ ሃይሎች ተሳክቶላቸው አያውቅም ብሏል።

ይህንን በመረዳት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንና ምርጫን ለማደናቀፍ የሚቋምጡ የውጭ ኃይሎች እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ሊያነሱ እንደሚገባ ተናግሯል።

ሴራቸው የህዝቡን አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር እንጂ የሚያላላው እንዳልሆነም አሰረድቷል።

በተለይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለዘመናት ስንኖርበት ከነበርነው ድህነት የሚያላቅቀን ስለሆነ ከምንጊዜም ለስኬታማነቱ ተሳትፎአችንን ልናጠናክር ይገባል ብላል።

ለግድቡ ግንባታ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ቦንድ በመግዛትና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት በመሳተፍ የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱንም ተማሪው ጠቅሷል።

የህዳሴዉ ግድብ በኢትዮጵያዊያን  እየተገነባ በመሆኑ ከደም ስጋችን ጋር የተዋሃደ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ያለችው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ አቅርቦትና አከባቢ ምህንድስና የአራተኛ ዓመት ተማሪ የትምወርቅ ክብሩ ናት።

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ 86 በመቶ እያበረከተች  ግብፅና ሱዳን ያለአግባብ በብቸኝነት ለዘመናት መጠቀማቸው እንዳስቆጫት ተናግራለች።

ከፍርደ ገምድል አስተሳሰብ ያልተላቀቁ ግብፅ፣ ሱዳን፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ  እንዲያነሱ ጠይቃለች።

በቱሪዝም ሀብት አስተዳደር የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ዮናስ ፍቅረአብ በሰጠው አስተያየት፤  በምርጫ ለመሳተፍ የሚያበቃውን ካርድ መውሰዱን ገልጾ ለምርጫው ሰላማዊነትም የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም