ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመለከተ

ደሴ ፤ሰኔ 3/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና ቀሪው ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመለከተ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር  በደሴ ከተማ  የተገነቡ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ እንዳሉት፤ የህዳሴው ግድብ  ኢትዮዮጵያን ከጨለማና ድህነት የሚያላቅቅ የሁሉም ዜጋ  አሻራ ያረፈበት ብሔራዊ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ቢጓተትም በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር የለውጡ አመራር በቁርጠኝነት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እንዲደርስ እየሰራ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ ተፈጥሮ ባደለው ሀብት ምክንያታዊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳይሆን የውስጥና ውጭ ጠላቶች ለማደናቀፍ  እየሞከሩ መሆኑን ተናገረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳመለከቱት፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ  ተጠናቆ ስራ እንዲጀምር የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ  ጫፍ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ታሪካዊ ጠላቶችን በጋራ መመከት የሚጠበቅበት ወቅቱ አሁን ነው።

በጉጉት የሚጠበቀው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትና ቀሪው ግንባታው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ በባለቤትነት መንፈስ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

በተለይም ምሁራን፣ ዲያስፖራውና ሌላውም ዜጋ በሃላፊነት ስሜት በመንቀሰቃቀስ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከልም እንዲሁ።

የአባቶቻችን ታሪክ በጋራ ደግመን የሀገራችን ሉዓላዊነትና ጥቅም እናስከብራለን፤ የአማራ ክልል ህዝብም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ተቀናጅቶ የህዳሴ ግድቡን እውን ያደርጋል ብለዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫም ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት በተደራጀ አግባብ እየሰራ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው፤ የወሎ ህዝብ አንድነትና ሰላሙን ጠብቆ ትላልቅ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታና  ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቅቅ ምሁራን፣ ወጣቱና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉትን  ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በደሴ ከተማ  አንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ ከተገነቡ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራት፣ ቄራ አገልግሎት ማሻሻያ፣ የመጠጥ ውሃ ማስፋፊና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተመልክቷል።

በልማት ፕሮጀክቶቹ  ምረቃ ስነ-ስርዓት የፌደራል ፣ ክልል፣ ዞንና ከተማ አስተዳር ከፍተኛ አመራሮች፣  የሀይማት አባቶችና ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት ከደሴ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም