የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል ብሩህ ለማድረግ አበክረው እንደሚሰሩ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል ብሩህ ለማድረግ አበክረው እንደሚሰሩ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች አስታወቁ
ሀዋሳ ሚያዚያ ሰኔ 3/2013 (ኢዜአ) ወንድማማችነትና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም በማጠናከር የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ብሩህ ለማድረግ አበክረው ለመስራት ዝግጂ መሆናቸውን ብልጽግና ፓርቲን በመወከል በሲዳማ ክልል የሚወዳደሩ እጩዎች አስታወቁ።
የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት በሲዳማ ክልል ቦርቻ ወረዳ በይርባ ከተማ ዛሬ በድጋፍ ሰልፍ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂደዋል።
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት የቀረቡት አቶ ደሴ ዳልኬ በወቅቱ፤ እንዳሉት፤ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረውን ጭቆና ለመጣል በለውጥ ፈላጊው ህዝብ ትግል የተወለደው የብልጽግና ፓርቲ የህብረተሰቡን ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ አበክሮ ይሰራል።
በተለይ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ብሩህ ለማድረግ፣ ወንድማማችነትንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ፓርቲው ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል።
ምርጫ በመጣ ቁጥር የውስጥና ውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ህልውና ለመፈታተን እንደሚንቀሳቀሱ በማስገንዘብ ይህን ለመግታት የሲዳማ ህዝብ ቆራጥ አቋም እንዳለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንድጠናቀቅ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት በክልሉ በዴሴ የምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ናቸው።
ፓርቲው የኢትዮጵያ የቀጣይ ዘመን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲን ለማስፈን እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ሃገሪቱን ወደ ከፍታ ሊያሻግር የሚችል አቅም አመቻችቶ ለምርጫው መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የክልሉ ህዝብ ፓርቲውን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በእጅ አዙር በማሰማራት የምርጫውን ሂደት ለማወክ የሚሰሩ ሃይሎችን ለመመከት ሁሉም ለሀገሩ ዘብ እንዲቆም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ባደረጉት ንግግር ፤ ፓርቲው የረዥም ዘመናት የህዝብ ጭቆና አዳምጦ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ድል ይበልጥ ጎምርቶና ፍሬ አፍርቶ የህዝብ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ህዝቡ በነቂስ በመውጣት በምርጫው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እያስመዘገበ ያለው የልማት ትሩፋትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የተናገረችው ደግሞ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ ወጣት ታየች ሲሳይ ናት።
ፓርቲው የሲዳማን ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄና የሴቶችን እኩል ተሳታፊነት ጥያቄ በመመለስ ረገድ ባለውለታ በመሆኑ በምርጫው ከጎኑ ለመሰለፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንድጠናቀቅ ወጣቶች ድርብ ሃላፊነት ያለብን በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ይጠበቅብናል ብላለች።
ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ አቶ ታደሰ ረቁዋ በበኩላቸው ፤በብልጽግና ፓርቲ ሃገሪቱ ወደ ከፍታ ማማ እየገሰገሰች በመሆኑ ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በሰልፉ መሳተፋቸወን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በሀገሪቱ የተለያዩ ጫናዎች ለማሳደር የሚመክሩ አንዳንድ የውጭ ሃገራት ከመንግስት ጎን በመቆም አጥብቀው እንደሚቃወሙም ገልጸዋል።
ሰልፈኞቹ ብልጽግናን መምረጥ የዴሞክራሲና ሰላም ጽኑ መሰረት መጣል ነው፣ የሴራ የተንኮል የደባና የሽብር ፖለቲካን አሸንፈን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ብልጽናግን ይምረጡ የሚሉ መልዕክቶቹን አስተላልፈዋል።