የምርጫ ጣቢያዎችን ለአካልጉዳተኞች ምቹ ማድረግ ይገባል - አካልጉዳተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ጣቢያዎችን ለአካልጉዳተኞች ምቹ ማድረግ ይገባል - አካልጉዳተኞች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ /2013 የምርጫ ጣቢያዎችን ለአካልጉዳተኞች የተመቹ በማድረግ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ የተለያዩ አካልጉዳተኞች ለኢዜአ ገለጹ።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን በሚያካሄዱት ክርክር ላይ ለአካልጉዳተኞች የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑም ተገልጿል ።
በመራጮች ምዝገባ ወቅት ለአካልጉዳተኞች ያልተመቹ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች እንደነበሩና ይህ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ሁኔታዎችን ማስተካከል እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አካልጉዳተኞች ተናግረዋል።
በምርጫ ምዝገባ ወቅት በአንዳንድ ጣቢያዎች ለአካልጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ እንደነበር ገልጸዋል።
ይህም አካልጉዳተኞች የህብረተሰቡ አካል መሆናቸውን በመገንዘብ በምርጫው እንዲሳተፉ የተደረገውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዳልነበሩ ነው ያወሱት።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የአካል ጉዳተኞችን ንቁ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
በመሆኑም በምርጫው እለት አካልጉዳተኞች በነጻነት መምረጥ እንዲችሉ ለማድረግ ምርጫ በሚደረግባቸው ጣቢያዎች ሁሉ ምቹ ሁኔታዎች ከወዲሁ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ታፈሰ ላከ"በምርጫ ምዝገባ ላይ እያየነዉ ያለዉ ነገር የአካል ጉዳተኞች ምቹ ሆነዉ ድምጽ እንዲሰጡ የድምጽ መስጫ ቦታዉ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆን እንቅስቃሴ እየተደረገ ነዉ፡፡ብለዋል።
ከፓለቲካ ፓርቲዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ፖሊሲዎች ብዙ አልሰማሁም ያለችው ደግሞ ወጣት ሰርካለም አዲስ ናት።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን በሚያደርጉት ውይይትና ቅስቀሳ አካልጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችና እቅዶች ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዳላካተቱ የገለጹት ደግሞ ወታደር አለም ደስታ ናቸው።
ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫ በኋላ በአገር ውስጥ ለሚከናወኑ ድርጊቶች አካልጉዳተኞች በሁሉም ላይ የመካተት ህጋዊ መብት እንዳላቸውም ያስረዳሉ።
በመሆኑም በመገናኛ ብዙኃን ላይ የፓለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳና ውይይት ለአካል ጉዳተኞች የሚሰሩትንና በእቅድ የያዙትንም ሊያቀርቡ ይገባል ብለዋል ።
የኢትዮጵያ አካልጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንደገለጹት፤ ምርጫው የአገር ሰላምና የዜጎች ደህንነትን የሚያረጋግጥ መሆን አለበት።
ለዚህም ሁሉም ማህበረሰብ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን በማድረግ አካልጉዳተኞች ይበልጥ ተጎጂ እንዳይሆኑ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የአካልጉዳተኞችን መብት ለማረጋገጥ አካልጉዳተኞች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው አቶ አባይነህ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ለዚህም አካልጉዳተኞች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሥርዓተ-ጾታ የማህበራዊ አካታች ባለሙያ አቶ ጥበቡ አለፋቸው እንደተናገሩት፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ አካልጉዳተኞች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም በሰው ኃይል በኩል ያለው እጥረት እንዲፈታ ሁሉም ደረጃውን የጠበቀና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።
ፓርቲዎች ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓም የምርጫ ቅስቀሳቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን፤ የድምጽ መስጫው ቀን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም መሆኑ ይታወቃል።