ቀጥታ፡

ተቋማቱ በመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ተባብረው ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ /2013 የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን ለማቀላጠፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመንገድ መሰረተ ልማት ሂደት ግንባታን ለማፋጠን ይረዳል ተብሏል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻህ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ ተፈራርመዋል፡፡

ዶክተር ቱሉ ስምምነቱ የባለሥልጣኑን ሥራዎች የሚያቀላጥፉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመንገዶች ግንባታን ለማፋጠን ያግዛል ብለዋል፡፡

አሰራሩን ቀልጣፋ ለማድረግም ዘመናዊ የቅየሳ ቴክኖሎጂዎችን በተለይም የአየር ላይ የቅየሳ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ገልጸዋል፡፡

መረጃን ለመሰብሰብ እስከ ሶስት ዓመታት ይፈጅ የነበረውን ጊዜ ወደ ስድስት ቀናት ለማሳጠር ያስችላልም ነው ያሉት፡፡

የሰው ኃይልና የገንዘብ ወጪ ለመቀነስ እንደሚረዳም ዶክተር ቱሉ አስታውቀዋል፡፡

ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ስምምነቱ ከሚያስገኘው ጥቅም አኳያ በፍጥነት ወደ ተግባር ለማስገባት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ መረጃ የማሰባሰቢያ መንገድ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም