ተቋማቱ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴዎች ለምርጫው ስኬታማነት መልካም መሆናቸውን አመላከቱ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴዎች ለምርጫው ስኬታማነት መልካም መሆናቸውን አመላከቱ
ሰኔ 3 / 2013 (ኢዜአ) ዓለም አቀፍ የቅድመ ምርጫን እንቅስቃሴ በመታዘብ የሚታወቁት ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩትና (አይ አር አይ) ናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንስቲትዩት (ኤን ዲ አይ) የተባሉ ተቋማት በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የቅድመ-ምርጫ እንቅስቃሴ በመዳሰስ ሪፖርታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ተቋማቱ እኤአ ከሚያዚያ 9 እስከ 26 በበይነ መረብ በመታገዝ ያደረጉትን ዳሰሳ እና ያገኙትን ውጤት መነሻ በማድረግ የታዘቡትን ችግሮችና ምክረ-ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡
ይህ ድርጅት በአሜሪካ የዓለም ልማት ድርጅት (ዩኤስ አይ ዲ) በጀት የሚደገፍ ሲሆን የቅድመ-ምርጫ ዳሰሳው የዓለም አቀፍ የምርጫ መመዘኛ ስታንዳርዶችን እና ስልቶችን መሰረት በማድረግ በዓለም የምርጫ ታዛቢዎች የስነ-ምግባር መመሪያ (ኮድ) መሰረት የተከናወነ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የሁለቱን ድርጅቶችን ጥምረት መሪ እና የቀድሞ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሀላፊ የነበሩት አምባሳደር ጆኒ ካርሰን በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉት የቅደመ-ምርጫ እንቅስቃሴዎች ምርጫው ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዕድል የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸው በዳሰሳቸው ወቅት ምርጫው እንዲካሄድ የሚፈልጉና የምርጫ ምህዳሩ እንዲሰፋ የሚፈልጉ አካላትን ማነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቶቹ ያከናወኑት የቅድመ-ምርጫ እንቅስቃሴ ዳሰሳ እና ትንተና ኢትዮጵያ ምርጫ ለማከናወን እየሰራች ያለችውን የቅድመ-ምርጫ ስራዎች ሊያጠናክሩ የሚችሉ ዓለም አቀፉ ትብብር እና ድጋፍ ስሜት እንደሚፈጥር በሪፖርቱ ተካቷል።
በሀገሪቱ እኤአ ከ2018 ወዲህ የመጣው ለውጥን ተከትሎ የዜጎች፣ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እና ብዙሃን መገናኛዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ማገዙን ያወሳል ሪፖርቱ በዚህም የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ይገድቡ የነበሩ የህግ ማዕቀፎች ማሻሻያ መደረጋቸውን ጠቁሟል።
ለዚህም እንደማሳያ የምርጫ ቦርድ ሀላፊ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትነት ሹመትን ለሴቶች መስጠቱ እንዲሁም ቀደም ሲል ታዋቂ የመንግስት ተቃዋሚ ለነበሩት ለህግ ባለሙያዋ ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሀላፊነትን ቦርዱ ገለልተኛ በመሆን ምርጫ የማስፈጸም አቅሙን በሂደት ማጎልበት እንደሚያስችለው እንዲሁ።
ምንም እንኳን ሪፖርቱ በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር መኖሩን፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ውክልና አናሳ መሆኑን፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች መዘግየትና የመሳሰሉ ችግሮች እንዳሉ ቢያመላክትም ምርጫው በቀጣይ ሀገሪቱ ለምታከናውነው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መሰረት ለመጣል መልካም አጋጣሚ እንዳለ አብራርቷል፡፡
በዚህም መሰረት ምርጫው ውጤታማ እንዲሆን በቅድመ ምርጫ ወቅት ባለድርሻ አካላት ማድረግ የሚገባቸውን 12 ምክረ-ሃሳቦችን ሰጥቷል፡፡
እነዚህም፡- የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በመቅረፍ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከምርጫ ቦርድ፣ ከድምጽ ሰጪዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ከተመራጮችና ከደጋፊዎቻቸው፣ ከሲቪክ ማህበራትና ትምህርት ሰጪ ድርጅቶች እንዲሁም ከታዛቢዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው፤
የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት በገለልተኝነት እና በምርጫው ላይ ጣልቃ ባለመግባት ስራዎቻቸውን እንደሚሰሩ ለህዝቡ ቁርጠኝነታቸውን ቢገልጹ፤ በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ-ምግባር ደንቡን በማክበር መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ጥሰው ሲገኙም እርምጃ በመውሰድ ከግጭት እና ከጥላቻ ንግግር በመራቅ ሰላምን ብቻ ለህዝባቸው መስበክ እንዲሁም የሰላም ጥሪ ለህዝቡ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው፤
በምርጫ ቦርድና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ግልጽ ውይይት በማድረግ ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ ለዚህም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በቅርበት መስራት፤ በቅድመ-ምርጫው ወቅት የኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮሎች ተግባራዊ እንዲደረጉ በግልጽ መንገር እንደሚያስፈልግ፤
ሴቶች በምርጫው ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ለምርጫ ቦርድ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማቅረብ ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸው፤
በሀገሪቱ የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዙጎች በምርጫው ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፤
ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት እምነት ማግኘት የሚያስችሉትን ተግባራት ከህግ ወጣ ባለ መልኩም ቢሆን እንደ የመራጮች ምዝገባ መረጃ እና መሰል መረጃዎች ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሲቪክ ማህበረሰቡ ትክክለኛ መረጃ ማሰራጨት የሚጠበቅበት መሆኑ፤
የሲቪክ ማህበራት ዜጎችን በማስተማር እና ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማንቃት በምርጫው ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንዳለባቸው፤
የግልም ሆነ የህዝብ (የመንግስት) ብዙሃን መገናኛ ተቋማት ሚዛናዊ የሆነ የምርጫ ዘገባ ሽፋን በመስጠት እንዲሁም የተሳሳቱ መረጃዎችን በማጣራት ሰዎች በተሳሳተ መረጃ እንዳይታለሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው እንዲሁም የብዝሃን መገናኛዎችም ሆኑ ጋዜጠኞች የምርጫ ሂደትና ውጤትን የተመለከተ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች የተረጋጋጠ መረጃ ብቻ ለህዝብ በማድረስ ድርብ ሀላፊነት እንዳላቸው አውቀው በዚህ አግባብ እንዲሰሩ ማድረግ፤
በተጨማሪም በምርጫ ቀንና በምርጫ ማግስት ደግሞ፤ የምርጫ ታዛቢዎች የምርጫ ሂደቱን ያለገደብ እንዲታዘቡ እና ትዝብታቸውን እንዲገልጹ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ በምርጫው ላይ በተለይ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ታዛቢዎች ቢሰማሩ የምርጫው ውጤት ተዓማኒነት ላይ ለዘጎች መተማመኛ እንደሚሆን መግለጹ፤
ታዛቢዎች በምርጫ ወቅት የታዘቡትን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ምርጫ ቦርድ ሁኔታዎችን ቢያመቻችላቸው መልካም መሆኑን፤ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤት ቆጠራ ሂደቱ አሳታፊ፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ማድረግ እንዳለበት፤
የህዝብ አመኔታን ለማግኘት ሲባል ምርጫ ቦርድ የምርጫ ድምጽ ቆጠራ ሂደቱ እንዴት እንደሚከናወን ለህዝቡ እና ለባለድርሻ አካላት መግለጫ መስጠት እንዳለበት፤
ለምርጫ ቆጠራ ቀን የሚያገለግሉ ሲሰተሞች በሙሉ ከምርጫ ድምጽ ቆጠራ በፊት መሞከር እንዳለባቸው፤
በአጠቃላይ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ለህዝብ ግልጽ መሆን ያለባቸውን መረጃዎች ሁሉ ተደራሽ ማድረግ በምርጫው በስኬት መጠናቀቅና ተዓማኒነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ በመሆናው በቀሩት ቀናት ጭምር በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ ምክረ-ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
በድርጅቶቹ የጠሰጡ ምክረ ሀሳቦችን በሙሉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሲሰራቸው እንደቆየ ለብዙሃን መገናኛዎች በሚሰጣቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ላይ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ድርጅቶቹ ከተመሰረቱበት እኤአ ከ1983 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ400 በላይ የቅድመ-ምርጫ ሂደቶችን በጋራ መታዘባቸው ተገልጿል፡፡