ቀጥታ፡

በኦሮሚያ እየተመረቁ ካሉ የመሰረተ ልማቶች ውስጥ 7ሺህ 500 ዎቹ በገጠር የተገነቡ ናቸው- ዶ/ር ግርማ አመንቴ

ነቀምቴ ሰኔ 03/2013 ( ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በዚህ አመት ተጠናቀው እየተመረቁ ካሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት ውስጥ 7ሺህ 500 ዎቹ በገጠር የተገነቡ መሆናቸውን በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ አስታወቁ።

በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በሊሙ ወረዳ በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ ያለውን የዋጃ ወንዝ የመስኖ ግድብ ግንባታ ዛሬ ጎብኝተዋል።

ዶክተር ግርማ በወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት ለህዝቡ ከፍተኛ ጠቄሜታ ያላቸውን የተለያዩ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ለመገንባት እያደረገ ባለው ጥረት በገጠር በልማት ዘርፍ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው።

በክልሉ በ2012 በጀት አመት በተለያዩ ዘርፎች  ግንባታቸው የተጠናቀቀ 6ሺህ  የመሰረተ  ልማት ተቋማት መመረቃቸውን  አስታውሰዋል ።

በመጠናቀቅ ላይ ባለው 2013 በጀት አመትም  ግንባታቸው የተጠናቀቀ ከ11 ሺህ በላይ የመሰረተ ልማት ተቋማት እየተመረቁ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዘንድሮ እየተመረቁ ካሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት ውስጥ 7ሺህ 500 ዎቹ በገጠር የተገነቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

በገጠር ከተገነቡ የመሰረተ ልማት ተቋማት መካከል የንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ የመንገድና የመስኖ ዋና ዋናቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ተቋማቱ በተለይም በአርብቶ አደር አከባቢ ትኩረት አድረገው መገንባታቸው የገጠር ልማት ዘርፉን ስኬታማ ያደረገው መሆኑን አስታውቀዋል ።

በገጠር ከተገነቡ አጠቃላይ የመሰረተ ልማት አውታሮች መካከል 50 በመቶ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሀ ተቋማቱ 1ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ  እንደሚያደርጉና 71 ነጥብ 7 በመቶ የነበረውን የክልሉን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 77 በመቶ እንደሚያሳድጉት አመላክተዋል።

በበጀት ዓመቱ 17 የመንገድ ተቋማትን ለማጠናቀቅ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ በ5 ቢሊዮን ብር ወጪ 15ቱ  ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ 80 የመስኖ ተቋማት  ግንባታቸው ተጠናቆ መመረቃቸውን ዶክተር ግርማ  አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የመሠረት ልማት ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ ወጭ  ከተደረገው 31 ቢሊዮን ብር ውስጥ 13 ቢሊዮን ብሩ ለገጠር መሠረተ ልማት ግንባታ መዋሉን ተናግረዋል ፡፡

ምዕራብ ኦሮሚያን የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ከቡልቡላ ቀጥሎ በነቀምቴ ግንባታው የተጀመረው ማዕከል ለምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች ሰፊ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ አመልክተዋል።

በአርጆ ዲዴሳና አንገር ወንዞች ላይ እየተገነባ ያለውን የመስኖ ግድብ በማጠናቀቅ  አርሶ አደሩ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት እየሰራ መሆኑን ዶክተር ግርማ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም