ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ እንዳትጠቀም የሚደርሰባትን ጫና ለመቀልበስ ምሁራን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል--ሚንስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ እንዳትጠቀም የሚደርሰባትን ጫና ለመቀልበስ ምሁራን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል--ሚንስቴሩ
ጎንደር ሰኔ 3/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ እንዳትጠቀም የሚደርስባትን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቀለበስ ምሁራን በሳይንሳዊ መረጃና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስገነዘበ፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በዓለም አቀፍ የውሃ ህጎች ላይ የሚመክር 9ኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ በጉባኤው ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ በፍትሃዊነት እንዳትጠቀም ግብጽና ሱዳን ለዓለም ማህበረሰብ የሚያቀርቡትን የተዛባና የተሳሳተ መረጃ ለመቀልበስ ምሁራን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የተሰማሩ ምሁራን ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ፍትሃዊ አጠቃቀም ለማስፈን እያደረገች ያለውን ጥረት በሳይንሳዊ መረጃዎች ሊደግፉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ምሁራን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የገነባቸው ግድብ ማንንም የማይጎዳ፤ ይልቁንም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የሚያስችል፤ፍትሃዊ አካሄድን የተከተለ መሆኑን በማስገንዘብ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛ መረጃ መስጠት እንዳለባቸው አመልክተዋል ።
"ምሁራን ግብጽና ሱዳን የአባይ ውሃ ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት እንዳላቸውና የሜዲትራኒያንና የቀይ ባሕር የውሃ አማራጭ መጠቀም እንደሚችሉ በጥናት የተደገፉ መረጃዎችን በማቅረብ ሊሟገቱ ይገባል" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ መጠን እንዲጨምርና ከደለል ስጋት ነጻ እንዲሆን እያከናወነች ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች በጥናትና ምርምር በማገዝና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማሳወቅ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
"ኢትዮጰያ የህዳሴው ግድብን 2ኛ ዙር ውሃ ሙሊት ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጓን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው "የግድቡን ውሀ ሙሌት ሊያስቆም የሚችል አንዳችም ሃይል የለም" ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና የድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ጉዳዮች የሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የህዳሴው ግድብ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት እስኪጠናቀቅ ድረስ ጫናው መቀጠሉ እንደማይቀር አመልክተዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በግድቡ ዙሪያ ድርድር ለሚያደርገው የመንግስት አካል በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ድጋፍ በመስጠት ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን እንዲጎናጸፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
"የውሃ ሙሊቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ጩኸቱም ይቀንሳል፤ ሱዳንና ግብጽም የግድቡን ጥቅም በመገንዘብ ከአፍራሽ አካሄዳቸው ይቆጠባሉ" ሲሉም አመላክተዋል።
"ግብጽና ሱዳን በህዳሴው ግድብ የሚያራምዱትን የተሳሳተ ትርክት ለመቀየር ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ናቸው፡፡
ምሁራን ለአህጉራዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በማፍለቅ ሀገራቱ በንግድና በምጣኔ ሀብት እንዲተሳሰሩ ለማድረግ ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡
በጉባኤው በዛሬው ውሎ በህዳሴው ግድብና ዓለም አቀፍ የውሃ ህጎች፣ በአባይ ወንዝ ታሪካዊነት፣ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን የውሃ ድርድርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አራት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡
በጉባኤው ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ምሁራን፣ የውጭ ጉዳይ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርትና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴሮች እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎችና አመራሮች ተእየተሳተፉ ነው፡፡