ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች የህዳሴ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ

ሰኔ 02 / 2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነትና ጫና የህዳሴ ግድቡን ከዳር ለማድረስ እንቅፋት እንደማይሆንም ተናግረዋል።

ኢዜአ የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች ለግድቡ ግንባታ እያደረጉ ያለውን የቦንድ ግዢ ያለማቋረጥ እንደሚተገብሩት ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ ለሶስት ጊዜ ያህል በወር ደመወዛቸው ቦንድ የገዙት የደቡብ መንገዶች ባለሥልጣን ሰራተኛ ወይዘሮ እልፍነሽ ከበደ እንደገለጹት፤ ግድቡ እንዲስተጓጎል እየጣሩ ያሉ ሃይሎችን በጋራ መታገል ይገባል።

የውጭ ኃይሎች በኢትዮጰያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና ጫና በመፍጠር ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሥራ እንዲስተጓጎል እያደረጉ ያለው ሙከራ ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ ተንበርክካ እንደማታውቅ ካለመገንዘብ የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሙሉዓለም አበበ በበኩላቸው "የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትና ጫና ይበልጥ ያበረታናል እንጂ ግድባችንን ከመጨረስ ወደኋላ አያስቀረንም" ብለዋል።

ተግቶ በመስራት፣ እርስ በእርስ በመዋደድና የሕይወት መስዋእትነት እስከመክፈል ድረስ ለህዳሴው ግድብ እውን መሆን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ፡፡

"የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን ተባብረው ጫና እደያረጉብን ያሉት ሌሎችን ጎድተን ሳይሆን ከምንፈልግበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ እየጣርን በመሆናችን ነው" ያሉት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ አዱኛ አሰፋ ናቸው።

"ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ተምሳሌት በመሆኗ ቀና እንድትል አይፈለግም" ያሉት አቶ አዱኛ፤ የውጭ ሃይሎች እየፈጠሩት ያለው ጫና የተለመደ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፕሮጀክት በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ያላቸውን ድጋፍ ሳያቋርጡ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ባለሙያ አቶ ሰማን በድሩ በበኩላቸው "በአሁን ወቅት ያለውን የውጭ ጫና ለመመከት ሀገራዊ አንድነትና ትሥሥራችን ማጠናከር ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ባለሙያ አቶ አንበርብር ዓለመሥላሴ ግድቡ ለሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌት በዝግጅት ላይ መሆኑ እንደሚያኮራቸው ገልፀው፤ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም