ቀጥታ፡

ባንኩ በ12 ማእከሎች ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተር ፕራይዞች የእውቀት ክህሎት ስልጠና እየሰጠ ነው

ጅማ፣ ሰኔ 02/2013(ኢዜአ)---የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሀገሪቱ በ12 ማእከሎች ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የእውቀት ክህሎት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

ባንኩ በሀገሪቱ በሚገኙ 12 ማእከላት በቪዲዮ ኮንፍረንስ የታገዘ  2ኛ ዙር ስልጠና ዛሬ ጀምሯል።

ልማት ባንኩ በመጀመርያ ዙር በስምንት ማእከላት አሰልጥኖ ዛሬ ሁለተኛውን ዙር መጀመሩን የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት ስልጠናው በሰባት ርእሶች ተከፋፍሎ የሚሰጥ ሲሆን ከነዚህም የሂሳብ አያያዝ፣ የቢዝነስ አመራር፣ የገበያ ፖሊሲ የሚሉ ርዕሶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ዶክተር ዮሀንስ አክለው "አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ ለማድረግና የስራ ፈጠራ እድሎች ከመፍጠር አንጻር ትልቅ ድርሻ አላቸው "ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በቪዲዮ ኮንፍረስን ባስተላለፉት መልእክት "የመንግስት የስራ አመራሮች መመዘን ያለባቸው ለወጣቶች በሚፈጥሩት ስራና የኢኮኖሚ ማሳለጥ መሆን አለበት" ብለዋል።

አቶ ሽመልስ አክለው "የሀገራችን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በብዛትና በጥራት በማምረት ለወጣቶች ስራ መፍጠርና ለገበያ በቂ ምርት ማቅረብ  አለባቸው" ብለዋል።

የጅማ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ጉርሙ ዶጫ በበኩላቸው " ባንኩ በአካባቢው ያሉ አነስተኛና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍና ለማበረታታት አሰራሮችን አጭርና ግልጽ አድርጓል" ሲሉ ተናግረዋል።

ባንኩ ያለመያዣ ገንዘብ በማበደር ስራ ፈጠራንና ኢኮኖሚውን በመደገፍ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጉርሙ አሁን ላይ ደግሞ የቢዝነስ እውቀት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ባንኩ ከዚህ በፊት ለአራት አመት ይረዝም የነበረውን የብድር ሂደት አሁን ላይ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማስተናገድ የሚቻልበት አሰራር ተግባራዊ  ማድረጉን አስታውቀዋል።

ስልጠናው እስከ ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም