የልማት ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት የሜካናይዜሽን እርሻ የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት የሜካናይዜሽን እርሻ የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ
ጎንደር ፣ ሰኔ 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት በሜካናይዜሽን የእርሻ ኢንቨስትመንት ትራክተሮችንና ኮምባይነሮችን መጠቀም ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
ዲስትሪክቱ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አንቀሳቃሾች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በጎንደር ከተማ ሲጀመር የዲስትሪክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ እሱባለው ሰቦቃ እንደተናገሩት፤ ባንኩ አሰራሩን በማዘመን በሜካናይዜሽን የእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ለመደገፍ ተዘጋጅቷል፡፡
ዘንድሮ በሊዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት የማምረቻ መሳሪያዎችን ለአንቀሳቃሾች ለማቅረብ በያዘው እቅድ መሰረት ከ272 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በምዕራብ ጎንደር ዞን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ውጤቶችን ለሚያመርቱ 40 ባለሀብቶች በሊዝ ፋይናንስ ኮምባይነሮችንና የእርሻ ትራክተሮችን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
"ባለፉት 20 ቀናት ብቻ በማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ግንባታ፣ ማዕድን ልማትና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ያቀረቡትን የ400 ሚሊዮን ብር የብድር ጥያቄ ባንኩ አፅድቋል" ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ አንዱአለም ሙሉ በበኩላቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ከስልጠናው የሚያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ከባንኩ የሚያኙትን ብድር ለታለመለት የልማት ዘርፍ እንዲያውሉ አስገንዝበዋል።
ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ስልጠና ላይ ከሰሜን፣ ደቡብ፣ ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ ከ250 በላይ አንቀሳቃሾች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
በቆይታቸውም በቢዝነስ እቅድ ዝግጅትና አስተዳደር፣ በሰው ሃብትና ፋይናንስ አመራር ዘርፍ በተግባር የተደገፈ የክህሎት ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተመልክቷል፡፡