የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችን አይቋረጥም- የመዲናዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችን አይቋረጥም- የመዲናዋ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 02 /2013 (ኢዜአ) የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ እስኪደርስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ግንባታውን ለማስተጓጎልና ለማስቆም ተደጋጋሚ ጥረት አድርገዋል።
የግድቡ ግንባታ ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በራስ አቅምና በህብረተሰብ ተሳትፎ ለአፍታ ሳይቋረጥ እየተከናወነ ይገኛል።
አሁን ላይ አጠቃላይ የግንባታው ክንውን 80 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚሉት ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት በመሆኑ እስከ ፍፃሜው ድጋፋቸው ይቀጥላል ።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው ሃብታችን በመሆኑ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የሚከፈለውን መስዋእትነት ተከፍሎ ካሁን በፊት ስናደርገው የነበረው የቦንድ ግዢ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ያሉት አቶ ታደሰ መላኩ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡
ወጣት ደጀኔ አብደላ በበኩሉ ካሁን በፊት ተደራጅቶ በሚሰራበት ማህበር በኩል የቦንድ ግዢና ማህበረሰቡ የማስተባበር ስራዎች መስራቱ አንስቶ የህዳሴ ግድብ ሙሌት ድጋፍ ለማድረግ አንድነት እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳል፡፡
ወጣት የካ መረጋ ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ የቦንድ ግዢ ተሳትፎ እንደነበረው ገልፆ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ጣልቃ ገብነት እንደሚያሳስበውና ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑ ይገልፃል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሃይሉ አብርሃም፤ ህብረተሰቡ የግድቡን መጠናቀቅ በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል ብለዋል።
የሁለተኛውን ዙር ውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የውጭ አገራት ጫና እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው ይህን ጫና ለመቋቋምና ግድቡን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ባለፉት 10 ወራትም የህዝቡና በተለይም የዳያስፖራው ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን ዶላር አውጥታ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ የ20 በመቶ ክንውን ይቀረዋል።
የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሁሉ ቀዳሚው ይሆናል።
የግድቡ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በዘንድሮው ክረምት እንደሚከናወን ይጠበቃል።