በመጀመሪያው ምእራፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት እናደርጋለን... ኩባንያው - ኢዜአ አማርኛ
በመጀመሪያው ምእራፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት እናደርጋለን... ኩባንያው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2013(ኢዜአ) በመጀመሪያ ምእራፍ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ 'የዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ 'ኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎች ተናገሩ።
በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ያገኘው 'ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ' ኩባንያ ስራ ለመጀመር የሚያስችለውን ስምምነት ትላንት ተፈራርሟል።
የስምምነት ፊርማው የተከናወነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የኬኒያው ፕሬዝዳነት ኡሁሩ ኬኒያታ በተገኙበት ነው።
የኢትዮጵያ ኮሙንኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ፤ ከቮዳኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻሚል ጆሱ፣ ከሳሪ ኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር እንዲንግዋ እንዲሁም ከሲሚቶሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማይሽ ማሂሽታ ጋር ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
በጥምረት ጫራታውን ካሸኑፉት ኩባንያዎች መካከል 56 በመቶ ድርሻ ያለው የኬኒያው የሳፋሪ ኮም ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፒተር እንዲንግዋ፤ አጠቃላይ የጫራታ ሂደቱ ግልጽና ተዓማኒ እንደነበር ተናግረዋል።
በቀጣይ የመጀመሪያ ምእራፍ ስራቸውም በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ እንደሚያተኩር ነው የጠቆሙት።
የሚያስፈልጋቸውን የሰው ኃይል ለማሟላትም ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ጋር በመቀራረብ የክህሎት ግንባታ ስራ እንደሚያከናውም ገልጸዋል።
በዘርፉ ተዓማኒና ተፎካካሪ ለመሆን ዝግጁ ነን ሱሉም ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያውያን የቢዝነስ አቅማቸውን በማጎልበት ለወደፊቱ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ እንደሚያግዙም አረጋግጠዋል።
የቮዳኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻሚል ጆሱ በበኩላቸው በመጀመሪያ ምእራፍ ስራቸው በርካታ የሀገሪቱን አከባቢዎች የሚሸፍን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም ኔትወርክ ማስፋፋት ላይ በስፋት መዋለ ንዋይ እንደሚያወጡ ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን በምናቀርባቸው የዲጂታል 'ፕላትፎርሞች' ተጠቅመው ምርቶቻቸውን በቀላሉ እንዲሸጡ በማድረግ ኑሯቸው እንዲሻሻል እናደርጋለን ብለዋል።
"ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ" የኬኒያው ሳፋሪ ኮም፣ የዩናይትድ ኪንግደም ቮዳፎንና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካውን ቮዳኮም፣ የጃፓኑን ሲሚቶምና ዲኤፍሲን በጥምረት የያዘ ኮባንያ ነው።
ኩባንያው ጫራታውን ያሸነፈበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ለመንግስት ገቢ ማድረጉን የኢትዮጵያ ከሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ለኢዜአ መግለፁ ይታወቃል።
ኩባንያው በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ ከ8 ቢለዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።