ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ በማር አቅርቦት ያላትን ተወዳዳሪነት ለመጨመር ይሰራል... ግብርና ሚኒስቴር

መቱ፡ ሰኔ 2/2013 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ በማር አቅርቦት ያላትን ተወዳዳሪነት ለመጨመር እንደሚሰራ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በመደበው 22 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በኢሉ አባቦር ዞን ያዮ ወረዳ የተገነባው የእናት ንብ ማራቢያና ማሰልጠኛ ማዕከል ትላንት ተመርቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ዮሐንስ በላይ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ማዕከሉ እንደ ሀገር የመጀመሪያው ነው።

ማእከሉ በአብዛኛው በባህላዊ ዘዴ ላይ የተመሰረተውን የንብ ማነብና የማር ምርት ሥራ በቴክኖሎጂ በመደገፍና በማዘመን ወደ ዘመናዊ ዘዴ ለማሸጋገር እንዲሁም የማር ምርት መጠንን ለማሳደግ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡


"ማእከሉ በተለይም በተፈጥሮ ማር ምርት እምቅ አቅም ላለው ለምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል" ብለዋል።


"ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላት አቅምና ለውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው የማር ምርት መጠን የማይመጣጠን በመሆኑ ምርቱን ለመጨመርና በዓለም ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለመጨመር በትኩረት ይሠራል" ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማት ኤጄንሲ ኃላፊ ዶክተር አሚናት አብዱራህማን በበኩላቸው ”ኦሮሚያን በማር ምርት ታዋቂ ለማድረግ አቅደን የተነሳንለትን ግብ ለማሳካት ማዕከሉ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው" ብለዋል።

እንደ ሀገርም የሚጠበቀውን የማር ምርት ለማሳደግ የተፈጥሮ ደን ባለቤት በሆነችው ያዮ በተገነባው ማዕከሉ እናት ንብን የማራባትና በንብ ማነብ ሥራ ላይ ገበሬዎችን ተቀብሎ የማሰልጠን ሥራ እንደሚሰራበት አስታውቀዋል ።

በኦሮሚያ ክልል ከ4 ሚሊዮን በላይ ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎዎች፣ እንዲሁም ከ 6 ሚሊዮን በላይ የንብ መንጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

"ይሁንና ስራው በቴክኖሎጂ ባለመደገፉና ከሙያ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት የሚጠበቀው ውጤት ባለመገኘቱ ማዕከሉ በግብዓቶችና በሰው ኃይል ተደራጅቶ ችግሮችን ለመቅረፍ ይሠራል" ብለዋል፡፡

የኢሉባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ፕሮጀክቶች አስተዳደር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መኮንን ባይሳ ለዞኑ ገበሬዎች ሁሉ "እንኳን ደስ አላችሁ" በማለት  ማዕከሉ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያስገኝ ዞኑ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ 

በኢሉባቦር ዞን በዓመት እስከ 25 ሺህ ቶን ማር ማምረት  የሚያስችል እምቅ አቅም መኖሩ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም