ቀጥታ፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ለ150 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2013(ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ ለ150 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ቁሳቁስ እየተጓጓዘ ነው።

የድምፅ መስጫ ቀን የስልጠና ቁሳቁስ ስርጭት በመጪዎቹ ሁለት ቀናት እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ የምርጫ ስራ የቁሳቁስ ዝግጅት ያለበትን ሁኔታ ለሚዲያ ባለሙያዎች አስጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሶሊያና ሽመልስ፤ ለ150 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች የስልጠና ቁሳቁሱ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እየተጓጓዘ ነው ብለዋል።

በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ለስልጠና የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ተሰራጭተው እንደሚጠናቀቁም ገልጸው፤ የምርጫ ቁሳቁስ በደረሰባቸው አካባቢዎች ስልጠናው እንደሚጀመርም ሃላፊዋ ተናግረዋል።

የስልጠና ቁሳቁሶቹን በማጓጓዝ ሂደት እስካሁን የገጠመ ችግር እንደሌለና የክልልና የፌደራል መንግስት ትብብር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከስልጠናው ቁሳቁስ በተጨማሪ ለምርጫ የሚያገለግሉ ሌሎች ቀላል የምርጫ ማስፈጸሚያዎች እየተጓጓዙ መሆኑንም አክለዋል።

ስልጠናው የሚካሄደው በየምርጫ ክልሉ ሲሆን ለስልጠናው ማስፈጸሚያ የሚውሉ በ3 ሺህ 800  ብሉ ቦክሶች ታሽገው ተልከዋል ነው ያሉት።

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች እየታሸጉ ያሉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችም ተጎብኝተዋል።

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም