በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰራተኞች መኖሪያና አገልግሎት መስጫዎች ተገንብተዋል-ኮርፖሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰራተኞች መኖሪያና አገልግሎት መስጫዎች ተገንብተዋል-ኮርፖሬሽኑ
ባህርዳር ሰኔ 02/2013 (ኢዜአ) በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰራተኞች መኖሪያና የሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ መከናወኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ፋብሪካው በ150 ሄክታር መሬት ላይ የፍራፍሬ ልማት በማካሄድ ለአካበቢው ማህበረሰብ ልምድና ተሞክሮ ለማስተላለፍ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ለኢዜአ እንዳሉት የመኖሪያ ቤትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ ግንባታ የአባቢውን የአየር ንብረት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተከናወነ ነው።
ከዋናው ፋብሪካ ግንባታ፣ ከሸንኮራ አገዳ ልማቱና ሌሎች ስራዎች ጎን ለጎን 2 ሺህ 50 የመኖሪያ ቤቶች በመገንባት ለሰራተኞች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተጨማሪም 24 የቢሮ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ህንጻዎችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል።
የመኖሪያ ቤትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ መገንባት ለፋብሪካው ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የባለቤትነት መንፈስ ለመፍጠር ማስቻሉን አስገንዝበዋል።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴ በበኩላቸው ፋብሪካው በ150 ሄክታር መሬት ላይ የብርቱካን፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና ሌሎች የፍራፍሬ ልማት ስራዎች እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የፍራፍሬ ልማቱ በዘመናዊ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ከልማቱ የተገኘው ውጤት አበረታች በመሆኑ ለጃዊና አካበቢው ማህበረሰብ ተሞክሮና ልምድ በማስተላለፍ ልምዱን ለማስፋት ታስቦ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።