በአባይ ተፋሰስ ላይ ለሚከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ግብፅና ሱዳን የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በአባይ ተፋሰስ ላይ ለሚከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ግብፅና ሱዳን የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው- ምሁራን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 2/2013 በአባይ ተፋሰስ ላይ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለውን የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ ግብፅና ሱዳን የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ማገዝ እንደሚገባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለይም ለሱዳን ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንዱና ዋነኛው ደለልና የጎርፍ አደጋን መከላከል ነው።
አገሮች ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሃብቶችን በጋራና በትብብር ማልማት ካልቻሉ ሃብቱ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ ሊሰጥ አይችልም ይላሉ የዘርፉ ምሁራን።
ኢትዮጵያ ባለፉት 40 ዓመታት በተለይም በአባይ ተፋሰስ ላይ የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።
የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱዳን የአባይ ወንዝ ዋነኛ ተጠቃሚ ቢሆኑም፤ ምንጩን በመጠበቅና በመንከባከብ በኩል ሚና የላቸውም ብለዋል።
የዓለም ትልቁ ፈተና የሆነውን ተለዋዋጭ የአየር ንብረትን ለመከላከል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ዋነኛ መፍትሄ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም በአባይ ተፋሰለስ ላይ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለውን የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ ግብፅና ሱዳን የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃና መሬት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጌቴ ዘለቀ
ለአባይ ተፋሰስ ኢትዮጵያ ለ40 ዓመት የሰራችውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሱዳንና ግብጽን እንዲከፍሏት በአለምአቀፍ ህግ መሰረት የመጠየቅ መብት አላት ብለዋል።
''እኛ ከፍተኛ ጉልበት ከፍተኛ ገንዘብ ሞቢላይዝ እያደረግን ነው። እነሱ እስከዛሬም በነጻ ነው ሲጠቀሙ የነበሩት ቀጣይ ደግሞ እዚህ ጋር እንክብካቤ ከሌለ ውሃውም ሊጠፋ ስለሚችል እንኳን የኛ ውሃ ተገደበ ሳይሆን፤በገንዘብም ጭምር ድጋፍ አድርገው እዚህ ጋር የአፈር ጥበቃ ስራ የውሃ እንክብካቤ የዛፍ ተከላ የሚደረገውን በሙሉ በገንዘብም ግብጽም ሱዳንም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገው እኛን ማገዝ አለባቸው።ያለው ደግሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያናው በዳሶ ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ኢትዮጵያ ደለልን ለመቀነስ ተራሮች ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት ሌሎች የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ምንም ሳይከፍሉ ነው እየተጠቀሙ ያሉት። ብለለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለ140 ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይገመታል።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በአግባቡ ከተሰራና ወደ ግድቡ የሚገባውን ደለል መከላከል ካልተቻለ የአገልግሎት ዕድሜው 375 ዓመታት ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሌላ በኩል በቂ የተፈጥሮ ሃብት ስራ ካልተሰራ የአባይ ውሃ መጠን በእጂጉ እየተመናመነ ሊሄድ ስለሚችል የተፋሰሱ አገሮች በጋራ ሊጠብቁት ይገባል ምሁራኑ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሥራ አመራር አካዳሚ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና በሆነበት ዓለም ላይ የተቀናጀ የአረንጓዴ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።'
ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገባውን ደለል 50 በመቶ መቀነስ ከተቻለ ግድቡ 140 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ይገመታል።
ለግድቡ 75 በመቶ የሚሆነውን ደለል ከተቀነሰ ከተቻለ ደግሞ 246 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይኖረዋል ይላሉ የዘርፉ ምሁራን።