በቴሌኮም ዘርፍ የሚፈጠረው ውድድር ሁሉንም ሴክተሮች የሚያነቃቃ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በቴሌኮም ዘርፍ የሚፈጠረው ውድድር ሁሉንም ሴክተሮች የሚያነቃቃ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
ሰኔ 1/2013 (ኢዜአ) በቴሌኮም ዘርፍ የሚፈጠረው ውድድር ሁሉንም ሴክተሮች የሚያነቃቃ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በበኩላቸው ሳፋሪ ኮም በኢትዮ ቴሌኮም ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባቱ ለሁለቱ አገሮች የልማት ትስስር የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ጨረታ ያሸነፈው ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ኩባንያ በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
የኢትዮጵያ ኮሙንኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ፤ ከቮዳኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻሚል ጆሱ፣ ከሳሪ ኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ኢድግዋ እንዲሁም ከሲሚቶሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማይሽ ማሂሽታ ጋር ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የኬኒያው ፕሬዝዳነት ኡሁሩ ኬኒያታ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር በቴሌኮም ዘርፍ የሚፈጠረው ውድድር ሁሉንም ሴክተሮች የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንተርኔት ተደራሽነት እንዲስፋፋ መደረጉ ደግሞ በግብርና፣ ትምህርት፣ የፈጠራ ስራዎችና ሌሎችም ዘርፎች መዘመን የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ፤ የኬኒያው ሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ ቴሌኮም ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባቱ ለሁለቱ አገሮች የልማት ትስስር የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ኪኒያ የቆየ የባህልና ታሪክ ትስስር እንዳላቸው ገልጸው በቴሌኮም ዘርፉ የተጀመረው የልማት ትስስርም ለበለጠ የትብብር ግንኙነት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ስራ የሚጀምረው ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ኩባንያ የስድስት ኩባንያዎች ጥምረት ሲሆን የኬኒያው ሳፋሪ ኮም 56 በመቶ ድርሻ አለው።
የኢትዮጵያና የኬኒያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1954 የኢትይጵያ ቆንስላ በኬኒያ ተከፍቶ መጀመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።