በሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል
ሰኔ 1/2013 ( ኢዜአ) በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።
በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ተቋማት እንዲተባበሩም ጥሪ ቀርቧል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጅአለም፤ በሰጡት መግለጫ በዞኑ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል።
ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ተፈናቃዮችን ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ድጋፉን ለመሰብሰብ የሚያግዝ ግብረ ሃይልና ንኡሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።
በእስካሁኑ እንቅስቃሴም ለተፈናቃዮች የእለት ደራሽ እርዳታን ከማቅረብ በተጨማሪ የፈረሱ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እየተሰባሰቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቤት መስሪያ ቁሳቁስ እየተሰባሰበ ሲሆን እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶችን መስራት የሚያስችል ቆርቆሮ ተገኝቷል ብለዋል።
የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ዋና ስራ አስፈፃሚና በአዲስ አበባ የተቋቋመው የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፋንታ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም መተጋገዝና መደጋገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
እስካሁን እየተደረገ ያለው ጥረት ዜጎቹን በዘላቂነት ለማቋቋም በቂ አለመሆኑንና ለዚህም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
ይህንን ገንዘብ ለማሰባሰብ የታሰበው በውጭም በሀገር ውስም ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መሆኑን ገልጸዋል።
በድጋፉ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች እንዲሁም ሁሉም ዜጋ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ አላማ የተከፈቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችም ይፋ ተደርገዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000399788181
በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ 1079601001041፣
በአባይ ባንክ 2012117396084010፣
በዳሽን ባንክ 5020809534011፣
በአቢሲኒያ ባንክ 66956466፣
በህብረት ባንክ 2210411629526018 በመለገስ ሁሉም ለዚህ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።
በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ድጋፍ ማድረግ ለሚሹ ሁሉ በየአገሩ ካሉ የኢትዮጵያ ከኢምባሲዎች ጋር በመነጋገር መለገስ ይችላሉ ተብሏል።