የጃፓኑ ሱምቶም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ በቴሌኮም ዘርፍ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የጃፓኑ ሱምቶም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ በቴሌኮም ዘርፍ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ገለጸ
ሰኔ 1/2013(ኢዜአ) በቴሌኮም ዘርፍ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ መንግስት በወሰደው ውሳኔ መሠረት ጨረታውን ያሸነፈው ‘የግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ ‘ድርጅት አንዱ የሆነው የጃፓኑ ሱምቶም፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ቶሽካዙ ናምቡ የኢንቨስትመንት ዕቅዳቸውን ያስታወቁት፤ በጃፓን የኢ.ፌ.ዲ.ረ አምባሳደር ካሣ ተክለብርሃን ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው።
ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ኮርፖሬሽናቸው ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ መንግስት በግልጸኝነት ባካሄደው የጨረታ ሂደት በማሸነፋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ካሣ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በጃፓን፣በኤሽያ እና በአፍሪካ ያለው የካበተ ልምድ በኢትዮጵያ ኢንቬስት በማድረግ እንዲደግመው ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል።