የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 01 /2013 (ኢዜአ) የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።
ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ የገቡት ለአንድ ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት መሆኑን ከኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፕሬዚዳንቱ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
የኬኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪይቸል ኦማሞ ትናነት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያና የኬኒያ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1954 የኢትዮጵያ ቆንስላ በኬኒያ ተከፍቶ ነበር የተጀመረው።
በመቀጠልም ኢትዮጵያ በ1961 የመጀመሪያውን አምባሳደር ወደ ኬኒያ የላከች ሲሆን ኬኒያ ደግሞ በ1967 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች።
ሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ያቋቋሙ ሲሆን የጋራ የድንበር አስተዳደር ኮሚሽን አቋቁመው በርካታ ውይይቶች ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሁለቱ አገራት መሪዎችም የሁለዮችሽ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር ተደጋጋሚ ጉብኝትና ውይይቶች ሲያደርጉ እንደቆዩም ይታወቃል።