ቀጥታ፡

በኦሮሚያ በሶስት ዞኖች በ204 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የመሰረተ ልማት ተቋማት ተመርቀው ለአገልግሎት ተዘጋጁ

ጊምቢ፣ ነቀምቴ፣ ነገሌ፣፣ ሰኔ1/2013(ኢዜአ)-በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩና ምእራብ ወለጋ እንዲሁም ጉጂ ዞኖች በ204 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የተገነቡ መሰረተ ልማት ተቋማት ተመርቀው ለአገልግሎት ተዘጋጁ።
በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን 99 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ተቋማትን የመረቁት በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አወሉ አብዲ ናቸው።

በዞኑ ግንባታቸው ተጠናቆ ከተመረቁት መካከል በሻምቡ ከተማ የ2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ፣ የዞኑ አስተዳደርና የሆሮ ወረዳ ፍርድ ቤት ጽህፈት ቤቶችና የሻምቡ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታዎች ይገኙበታል ።

አቶ አወሎ አብዲ በወቅቱ እንደገለጹት የሻምቡ ሆስፒታል ወደ ሪፌራል ሆስፒታል እንዲያድግና ሌሎች የዞኑ ህዝብ ያቀረባቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር እየተሰራ ነው ።

“በህዝቡ ጥያቄ መሰረት አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ ተገንብተው ለምረቃ በቅተዋል” ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ደቻሣ ናቸው። 
በተመሳሳይ በምእራብ ወለጋ ዞን በኖሌ ካባ ወረዳ በ31 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ሁማታ ተመርቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርገዋል ።

በወረዳው ተመርቀው ለአገልግሎት ከተዘጋጁት መካከል የገጠር የጠጠር መንገድና ዘመናዊ የገበያ ማእከል ይገኙበታል።
በጉጂ ዞን አናሶራ ወረዳ በይርባ ሙዳ ከተማም በ74 ሚሊዮን ብር በግንባታ ላይ ያለው የቴክኒክና ሙያ ማሰልኛ ኮሌጅ በከፊል ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል ።

የቴክኒክና ሙያ ኮሌጁ የግንባታ አካል የሆኑ 20 የመማርያ፣ የአስተዳደርና የቤተ መጽሀፍት አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርገዋል ።
ኮሌጁ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆና የውስጥ ቁሳቁስ ተሟልቶለት ስራ ሲጀምር ከ1 ሺህ በላይ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን የመቀበል አቅም እንደሚኖረው ተገልጻል ።

ኮሌጁን የመረቁት የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ “የለውጥ አመራሩ የህዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጀ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም