ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ላይ በተቃጡ ወረራዎች ሁሉ ባንዳዎች የአገርን ጥቅም አሳልፈው ሊሰጡ የሞከሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው -ታዋቂ ግለሰቦች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 01 /2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ወረራዎች ሁሉ ባንዳዎች የአገርን ጥቅም አሳልፈው ሊሰጡ የሞከሩበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ታዋቂ ግለሰቦች ገለጹ።

ባዕዳን ወራሪዎች ኢትዮጵያን ሲያጠቁና የተለያዩ ጫናዎችን ሲፈጥሩባት የቆዩት የውስጥ ባንዳዎችን እንደ ጋሻ በመጠቀም እንደነበርም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን የጣና በለስ ቁጥር-1 ስኳር ፋብሪካን ባስመረቁበት ወቅት ኢትዮጵያ ለብልጽግና ስትነሳ ''አንድም ከባንዳዎች አሊያም ከባዳዎች ሁለት ፈተና ይገጥማታል'' ማለታቸው የሚታወስ ነው።

''ባንዳዎች ዛሬም እንደ ጣሊያን ጊዜ አገራቸውን ካልሸጡ፣ ካልለወጡ ሥራ የሰሩ ስለማይመስላቸው የኢትዮጵያ ብልጽግና ድክመቶች ሆነው ተለይተዋል'' ብለዋል በንግግራቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ባዳዎችም ከውጪ ሆነው ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል ይሰራሉ፤ ኢትዮጵያውያን ባዳዎችን ከመታገላችን በፊት ባንዳዎችን ማጥራትና ማስቆም ግዴታ ነው'' ብለዋል።

ይህንኑ ጉዳይ ኢዜአ ከኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት አንጻር ለመቃኘት ከሁለት ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት፣ ደራሲና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል ጌታቸው በለጠ፤ ኢትዮጵያ በዘመኗ ሁሉ በባንዳና በባዕዳን ተፈትናለች ይላሉ።

ከሁሉም በላይ ግን አሁን ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ የከተታት የውስጥ ጥንካሬዋ መዳከሙ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በብዙ መመዘኛ ሲታይም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር የባንዳዎችና የባዕዳን ግፊት ነው ይላሉ።

መሰል ክስተቶች አዲስ ሳይሆኑ በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ሲፈትኗት የቆዩ ተግባርና ድርጊቶች መሆናቸውንም ይገልጻሉ።

አቶ ጌታቸው ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በነበረው የኢጣሊያ ወረራ ወቅት የነበረውን የባንዳዎች ሴራ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ጣሊያንን ድል ካደረገች በኋላ በአገር ሻጭነት የተፈረጁ የውስጥ ባንዳዎች እንደ ድል አድራጊ ለሽልማት ራሳቸውን አጭተው ነበረም ይላሉ።

በተመሳሳይ በደርግ ዘመነ መንግስት በውስጥ ባንዳዎች ተሳትፎ ከፍተኛ ሠራዊት የነበረው መንግስት ለሽንፈት መዳረጉን አስታውሰዋል።

"በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት እንዲሁ ባንዳዎች አገርን ሩቅ ከሚወስዱ ተግባራት ይልቅ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እንዲተኮር አድርገዋል" ነው ያሉት።

አቶ ጌታቸው አክለውም በአገር ላይ የሚመጣውን አደጋ ለመከላከል ከሁሉም በላይ የምሁራን ድርሻ ትልቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕራይም ሚዲያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ፤ አገር ይቀጥል ዘንድ የባንዳም የሆነ የባዕዳ ሁኔታ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል ይላሉ።

የኢትዮጵያን ታሪክ ዋቢ አድርገው እንደገለጹትም በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ወረራዎች ሲቃኙ በአመዛኙ ባንዳዎች የአገርን ጥቅም አሳልፈው ሊሰጡ የሞከሩበት ጊዜ ብዙ ነበር።

በመሆኑም ''ባዳዎቹም ሆኑ ባንዳዎቹ የአገርን አንድነት እንዳያፈርሱና ከሌሎች አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳያሻክሩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል'' ብለዋል።

ይህን ሥራ ደግሞ የመሪዎች ወይም የምሁራን ሥራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ በትብብር መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

''ሁሉም ዜጋ የአገሩ ባለቤት ነውና በእነዚህም ሆነ በሌሎች ሀይሎች ኢትዮጵያ አንድነቷ እንዳይጎዳ፣ ጣልቃ ገብነቱ ገፍቶ ችግር እንዳያመጣ የጋራ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል'' ነው ያሉት ዶክተር ብርሃኑ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም