ለመተከል ዞን ተፈናቃዮች የምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለመተከል ዞን ተፈናቃዮች የምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ
ሰኔ 01 /2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በጸጥታ ችግር ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ።
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከተጠሪ ተቋማትና የተለያዩ አካላት ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ተከናውኗል።
ከተሰበሰበው 137 ሺህ ኪሎ ግራም የህፃናት አልሚ ምግብ፣ የምግብ ዘይትና አልባሳት ውስጥ ለመተከል ዞን የተመደበውን 37 ሺህ ኪሎ ግራም ድጋፍ በጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የተመራ ልዑካን ቡድን በአካል ተገኝቶ አስረክቧል።
የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስትና የዞኑ አመራርና ሥራ ኃላፊዎች ድጋፉን ተረክበዋል።
መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሊያ፤ በመተከል፣ በትግራይና በአጣዬ ለተፈናቀሉ ወገኖች 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰት ግጭት ንብረት የወደመባቸውንና ተፈናቃዮችን ለመርዳት የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ አጎራባች ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሚኒስትሯ የተመራው ቡድን ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ በማድረጉም ምስጋና አቅርበዋል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የተፈናቃዮች ተወካዮች የአገር ሽማግሌዎች ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
በጠቅላላ 137 ሺህ ኪሎ ግራም ከሚሆነው ድጋፍ ውስጥ 66 ሺህ ኪሎ ግራም ለመቀሌ፣ 35 ሺህ ኪሎ ግራም ለአጣዬ መመደቡ እንደተገለጸ ይታወሳል።
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በባህልና ቱሪዝም እንዲሁም በጤና ሚኒስቴር በኩል የተሰበሰበውን ደጋፍ በየአካባቢው ለዜጎች በማድረሱ ሂደት ሚኒስትሮቹ ያስተባብራሉ።
በዚህም የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ወደ ትግራይ የሚላከውን ድጋፍ ሲያስተባብሩ ወደ አጣዬ የሚላከውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስተሯ ዶከተር ሂሩት ካሳው እንዲሁም ወደ መተከል የሚላከውን ደግሞ የጤና ሚኒስሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ያስተባብራሉ።