ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምረጡኝ ቅስቀሳ የተመቻቸላቸውን ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ እየተጠቀሙበት አይደለም- ሚዲያዎች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 1/2013 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምረጡኝ ቅስቀሳና የፓርቲያቸውን አላማ ለማስተዋወቅ የተመቻቸላቸውን ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የሚዲያ ሃላፊዎች ገለጹ።
የስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን መራዘሙን ተከትሎ ከመጋቢት 30 ቀን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ለምረጡኝ ቅስቀሳ የተመደበው ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ለተጨማሪ 12 ቀናት መራዘሙ የሚታወስ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የተራዘመውን ቀን ተጠቅመው መርሃ ግብራቸውን በማስተዋወቅ በኩል አሁንም ክፍተት እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የህትመትና ብሮድካስት ሚዲያ ሃላፊዎች ገልጸዋል።
በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ማስረሻ ደምሴ በጋዜጣው ለ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች 90 ኮለም የጋዜጣ አምድ እንደተመደበላቸው አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ እድሉ ከተመቻቸላቸው ፓርቲዎች መካከል የተመደበለትን አምድ በትክክል የተጠቀመው አንድ ፓርቲ ብቻ መሆኑን ነው የገለጹት። 

ቀሪዎቹ የተመደበላቸውን አምድ በተሸራረፈ መንገድ መጠቀምና ከመጀመሪያው ጀምሮ ባለመጠቀማቸው ጋዜጣው አምዱን በባዶ ለማሳተም መገደዱን ተናግረዋል።
ፓርቲዎች የጋዜጣ አምድና የአየር ሰዓት እንዲጨመርላቸው በጠየቁት መሰረት ቢራዘምም አጠቃቀም ላይ መሻሸል አለመታየቱን ገልጸው በቀሩት ቀናት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል። 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የምርጫ ዴስክ ሃላፊ አቶ ገናናው ለገሰ በበኩላቸው ፓርቲዎች እስከ ግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በተቋሙ ከተመደበላቸው ከ10 ሺህ 50 ደቂቃ ውስጥ 6 ሺህ 700 ደቂቃውን ብቻ እንደተጠቀሙበት ገልጸዋል።

የሚያስተዋውቁትን ሃሳብ ወይንም ፖሊሲ በሰዓቱ አለማምጣት፣ የተመደበውን ሰዓት ሸራርፎ መጠቀምና ለተለያዩ ቋንቋዎች የተመደበውን አለመጠቀምና ሌሎች ከመራዘሙ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች አሁንም መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች በቋንቋዎች ቻናል፤ ክልል አቀፍ ፓርቲዎች ደግሞ እንደ አጠቃላይ የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት በትክከል የመጠቀም ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተመደበላቸው የጋዜጣ አምድ ልክ ሃሳባቸውን መጥኖ አለማቅረብ፣ የሚተላለፍላቸውን ሃሳብ በወቅቱ አለማቅረብና የፕሮዳክሽን ጥራት ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ መሆናቸውን ሃላፊዎቹ አስረድተዋል።

የምርጫ ህግንና የመገናኛ ብዙሃንን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ በማክበር በኩል ግን ከሌላው ጊዜ የተሻለ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የህዳሴ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ኢንጂነር ሱራፌል እሸቱ፤ ጭማሪ ከመደረጉ በፊት የህትመት ሚዲያዎችን ከመጠቀም አንጻር ክፍተት እንደነበረ ገልጸው ለተጨማሪ ቀናት የተራዘመውን በአግባቡ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ዘላለም ወርቅአገኘ በበኩላቸው ፓርቲው የተወሰነ የቋንቋ ገደብ ቢኖርበትም የተመደበለትን የአየር ሰዓት 90 በመቶ መጠቀሙን ተናግረዋል።

ለፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ለተጨማሪ ቀናት የተራዘመው ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

የዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫው እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም