ቀጥታ፡

የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በአጭር ጊዜ ስኬታማ መሆኑ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 1/2013 የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በአጭር ጊዜ ስኬታማ በመሆን እየሰጠ ያለው አገልግሎት አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የድርጅቱን የስራ አፈፃፀምና ለቀጣዩ 10 ዓመታት ለመተግበር ያዘጋጀውን ዕቅድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ተሰጥቷል።


የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር  ፍሬሕይወት ትልቁ፤ መሪ እቅዱንና አጠቃላይ የስራ ክንውኑን በሚመለከት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።


ድርጅቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት 2007 ዓ.ም ጀምሮ እየሰጠ ያለውን አገልገሎትና ያስመዘገባቸውን ውጤቶችም አብራርተዋል።


ከዚህ በመነሳትም ድርጅቱ የ10 ዓመት መሪ እቅዱን ማዘጋጀቱን ገልጸው አገልግሎቱን ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ዳኤማ፤ ድርጅቱ በአገልግሎት አሰጣጡ ስኬት የላቀ የጥራት የምስክር ወረቀት ተሸላሚ በመሆኑ አድንቀዋል።


የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አገልግሎት መስጠት የጀመረበት ጊዜ አጭር ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት በሚያካሂደው የለውጥ ስራ ከስኬታማ ተቋማት መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም አንስተዋል።

በአጭር ጊዜ ስኬታማ በመሆን እየሰጠ ያለው የህዝብ አገልግሎት ሌሎች ተቋማትም በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።


ድርጅቱ የአስር አመት መሪ እቅድ በማዘጋጀት በውጤታማነቱ ለመቀጠል የጀመረው ጥረትም የሚደነቅ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አንስተዋል።


በመጋቢት 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ ተመስርቶ የተሻለ አፈፃፀም ለነበራቸው እውቅና ሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ 10 የፌዴራል መንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደታቸው እውቅና ሲሰጣቸው የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በተሻለ መልኩ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት በመቻሉ ልዩ ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ቲቪ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ደግሞ የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚዎች ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም