ቀጥታ፡

እየሰራን ስራዎቻችንን እየዘከርን ለትውልድ አሻራ መተውያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ

ግንቦት 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) “እየሰራን ስራዎቻችንን እየዘከርን ለትውልዱም አሻራ እየተውን መሄድ ያስፈልጋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሶስት አመታት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጓቸውን ንግግሮች የያዘ ''አሻራ'' የተሰኘ መፅሃፍ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አማካኝነት ታትሞ ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ባደረጉት ንግግር “እየሰራን ካልሆነ ከአሻራ ጋር ልንገናኝ አንችልም” ብለዋል።
“አሻራ ስራ ስለሚፈልግ በየዕለቱ እየሰራን ስራዎቻችን ለትውልድ የሚተላለፉበትን ነገር እየፈጠርን ከሄድን በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ የምናስበውን ብልጽግና ማረጋገጥ ትችላለች” ሲሉ ገልጸዋል።
ብዙ ሰዎች ባለፉት ሶስት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያነሷቸው መፈናቀል፣ ግጭት፣ ጦርነት፣ ኮሮና፣ አንበጣ፣ ጎርፍና አለመረጋጋት ችግርና ፈተና እንደነበሩ ተናግረዋል።
ነገር ግን በነዚህ አለመረጋጋት በነበረባቸው ሶስት አመታት በንጽጽር ባለፉት 10 ዓመታት የተሰሩ ስራዎች የተሻሉ እንደነበሩ አስረድተዋል።
ለአብነትም ከሰባት ዓመታት በፊት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ 10 ትላልቅ የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ ስምንቱን ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።
ከስምንቱ መካከል ሰባቱ ወደ ምርት መግባታቸውን ገልጸው፤ “ስምንተኛው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ተጠናቋል፤ ትልቁ ችግር አገዳ ነው” ብለዋል።
አገዳ ለማምረት ግድብ መስራትና ውሃ መያዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሳካ ስራ መሰራቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታዎችም ውጤት እንደተመዘገበ ገልጸዋል።
ውጤቱ “በንጽጽር የተሻለ ጊዜ ባልናቸው ወቅቶች ተጀምረው ሊጠናቀቁ ያልቻሉና በከፋ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ ስራዎችን ያመላክተናል” ብለዋል።
“ይህ የእሳቤ፣ የህልምና የትጋት ውጤት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ሀሳቦቻችንና ቃሎቻንን የምናከብራቸው ከሆነና ለዚያም የምንተጋ ከሆነ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ያልነውን ማሳካት ይቻላል” ብለዋል።
ይህንን ለመካድና እንዳልነበረ ለማየት መሞከር አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ “አሁን ብዙ ሰዎች እየመጣ ያለውን ተጨባጭ ለውጥ ማመንና መቀበል የሚቸገሩት አይናቸውን ጨፍነው ውስጣቸውን ስለሚያሳውሩ ነው” ብለዋል።
እንዲህ አይነት ነገር ለኢትዮጵያ ብልጽግና የማይጠቅም እንደሆነም ገልጸዋል።
የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ይበልጥ መትጋት እንዳለባቸውና ቀሪ ስራዎች ብዙ እንደሆኑ አመላክተዋል።
ታሪክ የአሸናፊዎች ብቻ ሳይሆን የእውነት ጠበቃ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጀመረውን ተግባር በማስቀጠል የላቀ ዕውቀትና ጥበብ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ንግግሮችና ቁም ነገሮችን በማሳተም ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም