በአዲስ አበባ የምግብ ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው የሸጡ 24 ድርጅቶች እርምጃ ተወሰደባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የምግብ ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው የሸጡ 24 ድርጅቶች እርምጃ ተወሰደባቸው
ግንቦት 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የምግብ ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል ሲሸጡ በተገኙ 24 ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታውቀ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ "ዛሬ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለነገ ጤና" በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን ዛሬ ተክብሯል።
የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ የበአሉ መከበር የምግብ ወለድ በሽታዎች ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በሽታው ሲከሰትም በቀላሉ ለመለየት እንዲሁም የከፋ ችግር ሳያስከትል ለመቆጣጠርና እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት ስጋት የሆነው ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር በመደባለቅ ለገበያ ማቅረብ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከባዕድ ነገር ጋር በመደባለቅ ለገበያ እየቀረቡ ካሉ ምግቦች መካከል እንጀራ፣ ቅቤ፣ በርበሬና ማር እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።
ምግቦቹ ወቅት ጠብቀው ለገበያ እንደሚቀርቡ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ "የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተደረገ ክትትል በአዲስ አበባ 24 ድርጅቶች ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው በመገኘታቸው ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል" ብለዋል።
በአራት ክፍለ ከተሞች በተደረገ ክትትል 3 ሺህ 360 ኪሎ ግራም ቅቤ፣ 480 ኩንታል በርበሬ እና ከ1 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ከቅቤ ጋር ለማደባለቅ የሚውሉ የአትክልት ቅቤና የፓልም ዘይት መያዙን ገልጸዋል።
በዚህ ድርጊት ላይ የተገኙት ድርጅቶች የተዘጉ ሲሆን ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በእንዲህ አይነት እኩይ ተግባር ላይ የሚሳተፉትን የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም የተለያዩ አደረጃጀቶች መሰል ድርጊቶችን እንዲከላከሉና እንዲያወግዙ ዋና ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው "ዛሬ የሚሰራ የምግብ ደህንነት ለወደፊት እድገት መሰረት ነው" ብለዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ ምርት መጠቀም ከጤና ባለፈ ፈጣንና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ህገ ወጥ የምግብ ምርቶች ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት እንደሆኑ አስገንዝበው፤ ችግሩን ለመከላከል የህግ ማዕቀፎች፣ ደንብና መመሪያዎችን ማዘጋጀት መቻሉን ገልጸዋል።
የቅንጅት ሥራዎች አለመኖር እና የቁርጠኝነት ማነስ እንዳለ ገልጸው፤ በቀጣይ የቁጥጥር ስርአቱን ማጠናከርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዓለም ላይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደህንነቱን ባልጠበቀ ምግብ ሳቢያ ለበሽታ እንደሚጋለጡ የገለጹት ደግሞ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የምግብ ሳይንስና ስርአተ ምግብ ዳይሬክተሩ ዶክተር ማስረሻ ተሰማ ናቸው።
ከምግብ ደህንነት ጋር በተያያዘ ቤተሙከራዎችን አቋቁሞ በርካታ ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑንም አመልክተዋል።
"ኢንስቲትዩቱ በእንጀራና ዳቦ ውስጥ የሚጨመር ባእድ ነገርን በአጭር ጊዜ የሚለይ መመርመሪያ አዘጋጀቶ እውቅና አግኝቷል" ብለዋል።
በተጨማሪም ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናቶችን እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።