ቀጥታ፡

በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመፍታት ከግል አልሚዎች ጋር በመተባበር ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው

ግንቦት 30 /2013 (ኢዜአ) በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመፍታት ከግል አልሚዎች ጋር በመተባበር ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ገለጸ።

በአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መስከረም ዘውዴ በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባ ከ650 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበው መኖሪያ ቤት ለማግኝት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

መንግስት በየአመቱ መገንባት የቻለው የጋራ መኖሪያ ቤት ከ19 ሺህ የዘለለ ባለመሆኑ በፍጥነት የነዋሪውን ፍላጎ ለማሟላት እያዳገተ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግስት በሚያካሒደው የመኖሪያ ቤት ግንባታ የነዋሪውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት 30 ዓመታት ስለሚወስድበትና የፋይናንስ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የውጭ አልሚዎች የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በቤት ልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ከኤምባሲዎች ጋር በመሆን ቅድመ ሁኔታዎች ሲታዩ መቆየታቸውን አንስተዋል ።

በመሆኑም የገንዘብ አቅምና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ይዘው የሚመጡ አልሚዎች ተወዳድረው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በቤቶች ልማት ስራው ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል ብለዋል።

በቢሮው የግንባታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አርክቴክት ጃርሶ ጎሊሳ፤ በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማካሔድ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የተደረሰው ስምምነት ህጋዊ ሂደቶችን ተከትሎ የተፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው ፕሮፕርቲ 2000 የተባለ ኩባንያ የገንዘብ አቅምና ያለፉት አምስት አመታት የስራ አፈፃፀሙ መገምገሙን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኩባንያው  በራሱ ወጪ ቤቶችን ገንብቶ በአነስተኛ ወለድና ወጪ ለሕብረተሰቡ እንዲያስረክብ ለማስቻል ሒደቱን አልፎ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል ብለዋል።

ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ የነዋሪውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ሲሰራ የቆየ ሲሆን ኩባንያው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ 100 ሺህ ቤቶችን ገንብቶ እንዲያስረከብ እያንዳንዱ ሒደት በጥልቀት እየታየ መሆኑነም አብራርተዋል።

የፕሮፕርቲ 2000 የኢትዮጵያ ቢሮ ጀነራል ማኔጀር አቶ አበበ በላይ፤ ካንፓኒው ተገቢውን ሕጋዊ ሒደት አልፎ በግንባታው ለመሳተፍ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል ብለዋል።

የካንፓኒው አቅምና ልምድ አስመልክቶ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤንባሲን ጨምሮ በሀገር ውስጥ ባሉ አካላት ሲጣራ መቆየቱንም ጠቁመዋል።

ኩባንያው በሚቀጥሉት አምስት አመታት በ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር 500 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም