ቀጥታ፡

ምሁራን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

ግንቦት 30/2013 (ኢዜአ) ምሁራን ዘመናዊ ዲፕሎማሲን በመጠቀም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከፍ የሚያደርጉና ዕድገቷን የሚያፋጥኑ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው ተገለጸ።

የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች የምክክር መድረክ የምሁራን ሚና በዘመናዊ ዲፕሎማሲ፣ በብሄራዊ ማንነት፣ በህዳሴ ግድብና በወሰን ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሃብቶች ለዘላቂ ልማት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በመጠቀም  እያከናወነች ያለችውን የልማት ስራዎች ተከትሎ አንዳንድ  አገሮች ስራውን ከመደገፍ ይልቅ  እያደናቀፉ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

ይህ ድርጊት የአገሪቷ ሉዓላዊነት የሚገዳደር በመሆኑ በተለይ ምሁራን ዕውቀትና ብልጠት በተሞላበት አካሄድ ለመፍትሄው መትጋት አለባቸው  ተብሏል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች የምክክር መድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የአገር ሉዓላዊነትና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲዎችን ለማመንጨትና በስራ ላይ ለማዋል የሚደረገው ሂደት ላይ ተቀባይነት ያላቸውና የተሻሉ ሀሳቦችን ማፍለቅ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ምሁራን በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም ያልተገቡ ድርጊቶች ከማውገዝ ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ በማምጣት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ምሁራን ዘመናዊ ዲፕሎማሲን በመጠቀም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከፍ የሚያደርጉና ዕድገቷን የሚያፋጥኑ ስራዎችን ማከናወን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

በዘመናዊ ዲፕሎማሲ ዕውቀትና ብልጠትን በመጠቀም የአገርን ሉዓላዊነት ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን መስራት ይገባልዕ ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው የአገርን ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ የምሁራንና የዲፕሎማቶች ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

‘’ዲፕሎማሲ የአገርን ክብርና ብሄራዊ ጥቅም በብልሃት ከጦርነትና ከኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚያስጠብቅ ነው’’ ያሉት ዶክተር ሙሉ፣  ዩኒቨርሲቲዎች ብቁና ተወዳዳሪ ዲፕሎማቶችን በማፍራት ረገድ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የዲፕሎማሲ ሚና አገራዊና ዓለም ዓለም አቀፋዊ አዝማሚያዎችን ተከትሎ የአገርን ጥቅም ማስከበር መሆኑንም በመግለጽ። ነባራዊ ሁኔታን በሚመለከት የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የህግና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በዲፕሎማሲ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ህጎችን እንዲሁም መልካም ተሞክሮዎችን ያገናዘበ ጠንካራ የውጭ ግንኙነት ስራ ማከናወን አለባቸው ብለዋል።

ከውጭ የሚቃጡ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመቋቋም ምሁራንና ዲፕሎማቶች በተለያዩ አገሮች ያለውን ተሞክሮ ተጠቅመው መሞገት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

በተለይም አሜሪካ ኢትዮጵያ አሸባሪ ብላ ከፈረጀችው ድርጅት ጋር ድርድር ትቅረብ ማለቷን ተከትሎ የአሜሪው ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን የቀደመ ታሪክን ማንሳቱ ተገቢ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሃብቶችን ዓለም አቀፍ ህግን ተከትሎ ለዘላቂ ልማት ማዋል ለነገ እንደማይባል ተመልክቷል።

የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግድቦች ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም