ቀጥታ፡

ነጻ ሀገር ተረክበናል፣ ነጻ ሀገር እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እናስረክባለን---ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ግንቦት 30 /2013 (ኢዜአ) "ነጻ ሀገር ተረክበናል፣ ነጻ ሀገር እናስረክባለን፣ ድሃ ሀገር ተረክበናል የበለጸገች ኢትዮጵያን እናስረክባለን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ ከተማ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው "ደብሊው ኤ" የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተመርቋል፡፡

አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ታሪክ አውርሰውናል እኛም ለልጆቻችን ብልጽግናን በማውረስ የሚያኮራ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ስንዴ የማይለምን ትውልድ ለመፍጠር ሁላችንም በትብብር መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄሮች ቋንቋቸው ቢለያይ፣ ታሪካቸው የተለያያ ቢመስል ኢትዮጵያ በምትባል እቅፍ ውስጥ አብረን እስካለን ድረስ አንዳችን ለሌላችን መከታና ጋሻ እንጂ፣ ጠላት መሆን አንችልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከውጭ ኢትዮጵያን እየነቀነቁ ጠላት የመጣ እያስመሰሉ ጎጃምን ከወለጋ ለመለየት የሚጥሩ ኃይሎችን አውቀንባችኋል ብለን በጋራ መቆም እንጂ ጠላት መጣ ብለን መባላት የለበንም ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህብረትና በአንድነት ሀገሪቱን ማበልጸግና ነጻነቷን መጠበቅ አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከውጭ አገሪቱን እየነቀነቁ የሚያባሉንን ደግሞ በአንክሮ ማየት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን መበታተን ይቻላል በማለት አንዳንድ ግለሰቦች ሲናገሩ እንደሚደመጡ ጠቅሰው ኢትዮጵያን መበታተን ፍፁም አይቻልምም ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል ፡፡

"ኢትዮጵያን የሚበታትኑትን በታትነናቸዋል ወደፊትም እንበትናቸዋለን" ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ሌሎች ለእኛ ነጋሪ መስካሪ መሆን እንደማይችሉና አንድነታችንን እንደ ዘመኑ ጀግንነት በብልጽግና ላይ ለመድገም ሁሉም መተባበር አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡

ኢትዮጵያ ሶስት ምሰሶዎች አሏት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው ኢትዮጵያን የፈጠረ ያቆያትና የሚመራት ፈጣሪ፤ ሁለተኛው በክፉ ጊዜ ህይወቱን የሚሰዋ ኢትዮጵያን ለመጠበቅና ለማልማት ወደ ኋላ የማይለው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ሶስተኛው ደግሞ ከፈጣሪ የተሰጠን የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት ነው ብለዋል፡፡

እነዚሀን ሐብቶች ማልማት የሚችል ህዝብ ልበ ብርሃን የሆነ ህዝብ ፈጣሪውን የሚፈራና የሚያመልክ ህዝብ ስንሆን ኢትዮጵያን የሚገዛትም የሚያስቆማትም ኃይል በምድር ላይ አይኖርም ነው ያሉት።

የእኛ ኢትዮጵያውያን ዋነኛው አደጋ የፈጠረንን አምላክ አላማውን ስተን መጣላት ስንጀምር፣ አንድነት ስናጣ ኃብቶቻችንና ጸጋዎቻችንን ማልማት ሲሳነን ያኔ የሌሎች መሳለቂያ ልንሆን አንችላለን ብለዋል።

"ኢትዮጵያዊያን ፈጣሪ እንዳለን፣ አንድ መሆን እንዳለብን፣ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት እንዳለን ከተገነዘብን ለአለም ምሳሌና ረጂ እንጂ የማንም ሀገር መፈንጫ አንሆንም አንድነታችንን ሀብታችንን እንዲያበዛልን መትጋት አለብን" ብለዋለ፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋ በማውጣት ከአለም ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚቻልም ጠቅሰዋል፡፡

ህብረተሰቡ በፌስ ቡክ ከሚነዙ የውሸት መረጃዎች ራሱን በመጠበቅና ቆም ብሎ በማሰብ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመረቀው "ደብሊው ኤ" ኢንቨስትመንት ግሩፕ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ 

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም በቀን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ማምረት ይችላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም