ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን መበታተን ስለማይቻል አንድነታችንን ማጠናከር ይበጀናል- ዶክተር አብይ አህመድ

ባህርዳር ግንቦት 30 /2013 (ኢዜአ)- ኢትዮጵያን መበታተን የማይቻል በመሆኑ አንድነታችንን ማጠናከር ይበጀናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስገነዘቡ ::

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብረ ማርቆስ ከተማ በአንድ ባለሀብት በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተገነባውን   የ"ደብሊው ኤ" ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ዛሬ መርቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ማፍረስ  የማይቻል በመሆኑ አንድነታችንን በማጠናከር ብልጽግናችንን ልናረጋግጥ ይገባል።

ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሞክሩ ሀይሎች እንደማይቻላቸው በመገንዘብ ወደ አንድነት ሊመጡ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

"ባለሀብቶችን በመደገፍ እንዲሁም ሁላችንም እጅ ለእጅ በመያያዝና ጸጋዎቻችንን በአግባቡ በመጠቀም ብልጽግናችንን ማሳካት ይቻላል" ሲሉም ተናግረዋል።

የደብሊው ኤ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ወርቁ አይተነው በበኩላቸው "ፋብሪካው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በቂ ምርት በማምረት ሳይቆራረጥ ለገበያ ያቀርባል" ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ ምርቱን በተገቢው መንገድ ወደ ተጠቃሚ የሚያደርሱ አከፋፋዮች መለየታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ወርቁ እንዳሉት በ11 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ፋብሪካው በቀን 1 ሚሊዮን 350 ሺህ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም አለው ።

ፋብሪካው አሁን ላይ  ለ1ሺህ 500 ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቁመው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር እጥፍ የሰራ እድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

ፋብሪካው ዘይት በማምረት ለተጠቃሚዎች  ከማድረስ ባለፈ የአርሶ አደሩን የቅባት ምርት በመረከብ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥር አስታወቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣  የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣  የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የሲዳማ ክልል ርእሰ መሰተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞና ሌሎች ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም