የተጠርጣሪዎችን መብት በጠበቀ መልኩ ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ተከናውኗል ...ወንጀል ምርመራ ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
የተጠርጣሪዎችን መብት በጠበቀ መልኩ ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ተከናውኗል ...ወንጀል ምርመራ ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29/2013 ( ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብት በጠበቀ መልኩ የምርመራ ስራ ለማከናወን የሚያስችል የሪፎርም ስራ ማከናወኑን ገለጸ።
ቢሮው ያከናወናቸውን አጠቃላይ የሪፎርም ስራዎች አስመልክቶ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማብራሪያ ሰጥቷል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከለውጡ በኋላ በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
ከተቋም አደረጃጀት ጀምሮ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የምርመራ ስራዎችን በመዘርጋት በተጠርጣሪዎች ላይ ቀደም ሲል ይፈጸሙ የነበሩ በደሎችና የመብት ጥሰቶችን ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
የፖሊስን ስነ ምግባር ባልተከተለ መንገድ በተጠርጣሪዎች ላይ ይፈጸም የነበረው ያልተገባ አሰራርና ሀሰተኛ መረጃ በማደራጀት ተጠያቂ የማድረግ ህገ ወጥ ተግባርም እንዳይኖር ተደርጓል ብለዋል።
በግለሰቦችና በፖለቲካ ሹመኞች ጫና የፖሊስ የምርመራ መርህን ያልተከተለ ተግባር በተጠርጣሪዎች ላይ ይፈጸም እንደነበርም አስታውሰዋል።
በተለይ ‘’ማዕከላዊ‘’ በሚባለው ማቆያ በዜጎች ላይ ይፈፀም የነበረው አስከፊ ኢሰብአዊ ተግባር የተቋሙንና የአገሪቱን ገጽታ አበላሽቷል ብለዋል።
በመሆኑም ባለፉት ሶስት ዓመታት የተቋሙን ገጽታ ለመቀየርና ማዕከላዊን ወደ ሙዜየምነት ከመቀየር ባለፈ አዲስ ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራሮች መዘርጋታቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።
በፖለቲካ ወገንተኛና በጥቅም ትስስር ወንጀል እንዳይፈጸም አዲስ "የኢትዮጵያ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መመሪያ" ተግባራዊ በማድረግ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ተደርጓል።
አዲሱ መመሪያ ሳይንሳዊ የምርመራ ስልቶችን የሚከተል ሲሆን በተጠርጣሪዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር ያስችላል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም።
አዲሱ መመሪያ ከተጠርጣሪዎች መረጃን ለማግኘት ሃይል መጠቀምና ጨለማ ቤት ማስር እንዲሁም ሌሎች ኢሰብአዊ ተግባራትን በጥብቅ የሚከለክል መሆኑን ተናግረዋል።
ለምርመራ ከተዘጋጀ ቦታ ውጪ ተጠርጣሪዎችን መመርመርም ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተቋሙ የተሳካ የሪፎርም ተግባራት ለማከናወን ሃላፊዎችና ሰራተኞች ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት ተቋማትም ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ቢሮው በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሃይልና በተቋም አደረጃጀት የተሻለ በማድረግ የተጠርጣሪዎች መብት እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።
በምርመራ ወቅት ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይኖርም አዲስ አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራሉ።
በቀጣይም አሰራሩን ለማዘመንና በሳይንሳዊ አሰራር ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ለማስቻል የፎረንሲክ ምርመራ ላይ ልዩ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መአዛ አሸናፊ፤ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብረሃም በላይን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።