ኢዜማ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም በሚል ሀገር ለማፍረስ ከተሰለፉና ከሚሰሩ እኩይ ሃይሎች ጎን አይቆምም -ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም በሚል ሀገር ለማፍረስ ከተሰለፉና ከሚሰሩ እኩይ ሃይሎች ጎን አይቆምም -ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ
ጎንደር ፣ግንቦት 29/2013 (ኢዜአ) ለጊዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም በሚል ሀገር ለማፍረስ ከተሰለፉና ከሚሰሩ እኩይ ሃይሎች ጎን ፓርቲያቸው እንደማይቆም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ፡፡
ፓርቲው ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ዛሬ በጎንደር ከተማ የምርጫ ቅሰቀሳ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደተናገሩት ፓርቲው ለሀገሪቱ እድገትና ለህዘቦች አንድነት የተሻለ ነገር ይዞ ለመምጣት ከመስራት ውጪ ሀገር ከሚያፈርሱ ሃይሎች ጋር አይደራደርም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመፍጠር የምንታገለው ሀገር ሲኖር በመሆኑ በሀገር አንድነትና በህዝባችን ህልውና ላይ የሚቃጣን አደጋ ለመቀልበስ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጎን ፓርቲያቸው እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡
“የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ከተሰለፉ ሃይሎች ጋር ሆነን ሀገር እናድናለን እንጂ ሀገር የመበጥበጥ አቋም ፓርቲያችን የለውም” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለዚህ እኩይ ተልእኮም የተሰለፉ ሃይሎችን ፓርቲያቸው አጥብቆ እንደሚታገላቸው አስታውቀዋል፡፡
ፖለቲካና ዘርን ካቆራኘ የቀድሞ ስርአት የተላቀቀና ዜጎች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን በጋራ ለማበልጸግ የሚያደርጉትን ጥረት የሚደግፍ በዜግነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ስርአት መስፈን እንዳለበት የፓርቲያቸው አቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ የገበሬውን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ የመሬት ፖሊሲ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት የፓርቲያቸው አቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ገበሬውን ከገዛ መሬቱ አፈናቅሎ ጭሰኛ የሚያደርግ የመሬት ስሪት መቆም አለበት ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን በመድረኩ ገልጸዋል፡፡
ገበሬው የግል መሬቱን በመሰለው መንገድ እራሱንና ቤተሰቡን በሚጠቅም መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባው የፓርቲያቸው እምነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ያልተማከለ አስተዳደር መገለጫ በሆነው የፌደራሊዝም አወቃቀር ስርአት ፓርቲያቸው እንደሚያምን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራለዝም መተግበር እንዳለበት የፓርቲያቸው አቋም እንደሆነም ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ ፖሊሲ ዙሪያም የፓርቲያቸው መሰረታዊ ፍልስፍና ማህበራዊ ፍትህ እንደሆነ የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚያሟላ የኢኮኖሚ መዋቅር መፈጠር እንዳለበት የፓርቲያቸው እምነት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ህዝቡ የሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብ መዝኖና አገናዝቦ ነጻ በሆነ መንገድ መሪዎቹን ለመምረጥ መዘጋጀት እንዳለበት ያሳሰቡት ደግሞ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሃብታሙ ኪታባ ናቸው፡፡
የስልጣን ባለቤት ህዝቡ እንደመሆኑ የሃሳብ ልእልና መርህን በመከተል ዘመኑን የሚመጥን የፖለቲካ ስርአት በሀገሪቱ እንዲሰፍን ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ መድረክ ላይ ከጎንደር ከተማና አካባቢው የተውጣጡ ወጣቶች አርሶአደሮች የመንግስት ሰራተኞችና ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም የፓርቲው አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል፡፡