ቀጥታ፡

በክልሎች መካከል የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ፍትሓዊ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ

ግንቦት 29/2013 (ኢዜአ) በክልሎች መካከል የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ፍትሓዊ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ተናገሩ።

የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በ600 ሚሊዬን ብር ከገዛቸው የመንገድ ጥገና ማሽነሪዎች መካከል 21 'ሞተር ግሬደሮችን' ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች አስረክቧል።

በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ፤ መንግስት በክልሎች መካከል ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ በፊት ከፍተኛ ችግር ሆነው ከዘለቁት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይ ደግሞ የመንገድ መሰረተ ልማት አንድ የፖለቲካ የኢኮኖሚ ማሕበረስብ ለመፍጠር ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የማሕበረሰቡን መስተጋብሮች የማሳለጥና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመፍጠርም የመንገድ መሰረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም መሰል የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ካላቸው ትሩፋት አንፃር በፍትሃዊነት እንዲዘረጉ መንግስት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ለመንገድ ግንባታ የሚሰጠው ትኩረት ለመንገድ ጥገናም መሰጠት አለበት ብለዋል።

በዚህ ረገድ በዛሬው ዕለት ለክልል መንገድ ጽህፈት ቤቶችና ለከተማ አስተዳደር የተሰጡ ማሽነሪዎች ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካላት 145 ሺህ ኪሎ ሜትር የመንገድ ሽፋን በቀጣዮቹ አስር ዓመታት 100 ሺህ ኪሎ ሜትር ለመጨመር መታቀዱንም ገልጸዋል።

የልማት እቅዱ ሲሳካ የኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ይደርሳል ብለዋል።

ማሽነሪዎቹ የተከፋፈሉት በክልሎች በጀት ድልድል ቀመር መሰረት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የመንገድ ፈንድ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሀመድ ናቸው።

ጽህፈት ቤቱ በ600 ሚሊዬን ብር ከገዛቸው 21 ሞተር ግሬደርና 12 ቡልዶዘሮች መካከል ሞተር ግሬደሮቹን አስረክቧል።

ማሽነሪዎቹም የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በመንገድ ጥገና ዘርፍ የሚነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይረዳሉ ብለዋል።

ክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ በአገር ሀብት የተገዙ ማሽነሪዎችን ለትክክለኛው ዓላማ ብቻ በማዋል እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።

የመንገድ ፈንድ ፅህፈት ቤት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ዓመታዊ ገቢውን አሁን ካለበት 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወደ 14 ቢለዬን ብር ለማሳደግ ማቀዱንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም