ፌዴራል ፖሊስ አዲስ የወንጀል ምርመራ መመሪያ ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራል ፖሊስ አዲስ የወንጀል ምርመራ መመሪያ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ያከናወናቸውን አጠቃላይ የሪፎርም ስራዎች አስመልክቶ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማብራሪያ ሰጥቷል።
ቢሮው ባለፉት ዓመታት የተጠርጣሪዎች ማቆያ፣ ለተለያዩ ስራዎች የሚያገለግሉ ቢሮዎችና ሌሎችም ላይ የሪፎርም ስራዎችን አከናውኗል።
በዚሁ ማብራሪያም አዲስ "የኢትዮጵያ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መመሪያ" መዘጋጀቱም ተገልጿል።
አዲሱ መመሪያ ሳይንሳዊ የምርመራ ስልቶችን የሚከተል ሲሆን በተጠርጣሪዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር ያስችላል ተብሏል።
በኢትዮጵያ የወንጀል ምርመራ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተገናኘ ብዙ ክስና ወቀሳ የሚቀርብበት መሆኑን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተፈጠረው ለውጥ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱ ይታወቃል።
በዛሬው እለትም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲዘጋጅ የቆየው አዲስ የወንጀል ምርመራ መመሪያ ይፋ ሆኗል።
ቢሮው ያከናወናቸውን የሪፎርም ስራዎች በሚመለከት በሰጠው ማብራሪያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መአዛ አሸናፊ፤ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩና ሌሎች ሀላፊዎችም ተገኝተዋል።
በዛሬው እለት የወንጀል ምርመራ ቢሮ ለሚያስገነባው አዲስ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ እንደሚቀመጥም ይጠበቃል።