ቀጥታ፡

የግልገል በለስ - ጉባ 70 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ስራ ዳግም ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29/2013 ( ኢዜአ) በመተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር ተቋርጦ የነበረው የግልገል በለስ - ጉባ የ70 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ስራ ዳግም ተጀመረ።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፣ የዞኑ ከፍተኛ አመራርና ሌሎች አካላት የመንገዱን ስራ ዳግም መጀመር በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል።

የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ በዞኑ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታ ወደ ስራ እየገቡ መሆኑም ተጠቁሟል።

በዚህም ከግልገል በለስ ወደ ጉባ የሚወስደው የግልገል በለስ ጉባ 70 ኪሎ ሜትር የመንገድ  ግንባታ ፕሮጀክት ስራ ዳግም ተጀምሯል።

የግንባታ ስራውም በቻይናው ሬል ዌይ ነምበር ስሪ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ አማካኝነት እየተካሄደ ነው።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጸኃይ ቡየ፤ ዞኑ በጸጥታ ችግር ውስጥ መቆየቱን አንስተው ችግሩን ለመፍታት የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል የተሻለ ስራ መስራቱን ጠቁመዋል፡፡

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲገቡ መደረጉም ጥሩ ስኬት ተገኝቶበታል ብለዋል።

በዞኑ ለማልማት በዕቅድ ከተያዙት 43 ፕሮጀክቶች መካከል ከግልገል በለስ እስከ ጉባ ያለው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም መነሻ በማድረግ የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች የተደረገላቸውን ጥሪ ተከትሎ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አንተነህ፤ የመንገዱ ባለቤት ህዝቡ ስለሆነ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት በማስቀጠል ለፕሮጀክቱ ስኬት በጋራ ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ለህዳሴ ግድብ የሚጓጓዝ ግብዓት ያለምንም እንቅፋት እንዲደርስ ሰራዊቱ 24 ሰዓት ሙሉ በተጠንቀቅ እየሰራ እንደሚገኝ በምዕራብ ዕዝ የ22ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሰይፍ ኢንጊ ገልጸዋል።

በዞኑ የነበረው የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ ህብረተሰቡና የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች ወደ መደበኛ የስራ እንቅስቃሴ እየተመለሱ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ሰራተኞችም በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ተከትሎ ተቋርጦ የነበረው የመንገድ ግንባታ መጀመሩን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡን የሰላሙ ባለቤት ለማድረግም ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም