ኤምባሲው በጅቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
ኤምባሲው በጅቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያየ
ግንቦት 28/2013(ኢዜአ) በጅቡቲ የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በጅቡቲ ከሚገኙ የእምነት አባቶች፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመንግስት ተቋማት ቅርንጫፍ ተወካዮች፣ የኤምባሲው ሰራተኞችና ሌሎች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ትላንት በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂዷል።
በጅቡቲ የኢ.ፌ.ዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋየ በሀገራዊ ለውጡ፣ በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ተግባር፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር እንዲሁም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በጣለችው የጉዞ እገዳ ማዕቀብ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ለሀገራዊ ለውጡ መምጣት ምክንያት የሆኑትን ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች ፣ በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ ስኬቶችና የገጠሙ ተግዳሮቶች ላይይም ገለጻ አድርገዋል።
በሀገሪቱ ለውጡ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እየገጠሙ ላሉ ተግዳሮቶች ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ነው የገለጹት።
ህወሀት ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ህገወጥ ተግባራት ሲፈፅም መቆየቱንና በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል።
በተወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ህወሀት በአሁኑ ወቅት መደበኛ ሰራዊት የሌለው አሸባሪ ቡድን መሆኑን አውስተዋል፡፡
በትግራይ ክልል በመጀመሪያው ዙር 4.5 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሁም በሁለተኛው ዙር 2.7 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደተደረገላቸው የገለጹት አምባሳደር ብርሃኑ፤ከዚህም ውስጥ 70 በመቶ እርዳታ በመንግስት እንደተሸፈነ ተናግረዋል።
መንግስት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለመኖራቸው የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ምርመራ እያደረገ መሆኑንና የተጠረጠሩትን ወደ ህግ የማቅረብ ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ አምባሳደሩ ባደረጉት ገለፃ፣ ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ በፍትሀዊነትና በምክንያታዊነት የመጠቀም መርህ እንደምታራምድና ሁለተኛው ዙር የውሀ ሙሌት በቅርቡ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።
ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚደረጉ ድርድሮች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥሉ ኢትዮጵያ ፅኑ እምነት እንዳላትም ተናግረዋል ፡፡
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ባለው የድንበር ጉዳይ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት መውረሯንና በአርሶአደሮችና በንብረታቸው ላይ ጥቃት መፈፀሟን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ስደስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሜሪካ የተጣለው የጉዞ እገዳ ማዕቀብ በተሳሳተ መረጃ ላይ የተወሰደ ውሳኔ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ በራሷ ውስጣዊ ጉዳይ የማንንም ጣልቃገብነት እንደማትቀበል ተናግረዋል፡፡
የዳያስፖራ አባላት አንድነታቸውን በማጠናከር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን ከትክክለኛ ምንጭ በመውሰድ ለሌሎች በማስተላለፍና ለሀገሩ ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጅቡቲ ሊገነባ ለታሰበው የማህበረሰብ ት/ቤት ባለቤት በጀቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሁለገብ አስተዋፅኦ በማድረግ የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል ፡፡
ማንነትም፣ ክብርም፣ ስልጣንም የሚኖሩት ሀገር ስትኖር መሆኑን የተናገሩት የመድረክ ተሳታፊዎች፤ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጣልቃገብነትን መመከት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ ትክክለኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ለሀገራቸው ገፅታ ግንባታ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ጠቅሰው፤ የኮሚዩኒቲ ት/ቤቱ ግንባታ እውን እንዲሆንም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።