ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሩ ወደ ግብርና መካናይዜሽን አሰራር እንዲሻገር መንግስት ድጋፍ እያደረገ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ግንቦት 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሩ ከልማዳዊ የግብርና ዘዴ ተላቆ ወደ መካናይዜሽን አሰራር እንዲሻገር መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የለማውን የስንዴ ማሳ በመስክ ተመልክተዋል፡፡

በዚህ ወቅት የክልሉ ፕሬዚዳንት እንዳሉት፤ መንግስት አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ አልፎ ገበያን ማዕከል ያደረገ ልማት ላይ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በተለይ ከውጭ የሚገባውን  ስንዴ በሀገር ውስጥ መተካት እንዲቻል የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ ለማልማት የተያዘው እቅድ እንዲሳካ በስራ ለተሰማራው አርሶ አደሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከልማዳዊ የግብርና ዘዴ ተላቆ ወደ ግብርና መካናይዜሽን እንዲሻገር የትራክተር፣ ሌሎች ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችና ግብዓቶች ድጋፍ  እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ ፤  አርሶ አደሩም መንግስት እያመቻቸ በሚገኘው እድል በመጠቀም እራሱን መለወጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ከጊኒር ወረዳ ሀረዋ አንድ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አብዱልቃድር ሀሰን በሰጡት አስተያየት፤  የመንግስት ስራ ሃላፊዎች ጉብኝት በልማት ስራቸው እንዲተጉ ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ 

የመንግስት የስራ ኃላፊዎቹ አርሶ አደሩ በመደበኛው የበልግ ዝናብ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም በኩታ ገጠም የለማውን የስንዴ ማሳ በመመልከት  አርሶ አደሩን አበረታተዋል፡፡

በምስራቅ ባሌ ዞን በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከ109 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በስንዴ መልማቱና ቡቃያውም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ከዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ሉኡካን ትናንት በምስራቅ ባሌ ዞን ለገ ሂዳ ወረዳ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በብርሃን ለሁሉም ፕሮጄክት የተገነባውን የቤልቱና ባህማ ከተሞች በጸሐይ ኃይል የሚሰሩ ሁለት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ማዕከላት መርቀው ስራ ማስጀመራቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም