ቀጥታ፡

ለመኸር እርሻ የሚውል ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑ ተገለጸ

ግንቦት 28 /2013 (ኢዜአ) ለ2013/14 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ የሚውል ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ተጨማሪ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባም ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ ለ2013/14 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ የሚውሉ እንደ የሰብል ምርጥ ዘርና አግሮ ኬሚካሎች ያሉ የግብርና ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በምርት ዘመኑ ከ18 ሚሊዮን 169 ሺህ በላይ ኩንታል ዩሪያን ጨምሮ የተለያዩ የማዳበሪያ አይነቶችን ከውጭ ለማስገባት ያቀደው ኮርፖሬሽኑ፤ ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ከ15 ሚሊዮን 47 ሺህ በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ማድረስ መቻሉን አመልክቷል።

ከዚህ ውስጥ 12 ሚሊዮን 127 ሺህ 510 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ በሕብረት ሥራ ማህበራት አማካይነት ለአርሶ አደሩ እየተከፋፈለ መሆኑን አስታውቋል።

ቀሪው ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ በቀጣይ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

በምርጥ ዘር አቅርቦትም እስካሁን 284 ሺህ 437 ኩንታል የተለያዩ የዘር ደረጃቸውን የጠበቁ የሰብል ዘሮችን በኮርፖሬሽኑ እርሻዎች፣ በሰፋፊ የባለሃብቶች እርሻና በአርሶ አደሮች ማሳ በማምረትና በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እየተከፋፈለ ይገኛል።

በተመሳሳይ በሰብል ዘመኑ በኮርፖሬሽኑ እርሻዎች፣ በባለሃብቶች እርሻና በአርሶ አደሮች ማሳ 335 ሺህ 765 ኩንታል ተጨማሪ የተለያዩ የሰብል ዘሮችን ለማምረት ታቅዶ መሬት የማዘጋጀትና ዘር የመዝራት ሥራ እያካሄደ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

በዚሁ የዝግጅት አካል ለ2014/15 የሰብል ዘመን ለተጠቃሚዎች ዘር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም የጠቆመው መግለጫው፣ ለዚህም የኮርፖሬሽኑ 4 ሺህ 529 ሄክታር መሬት ታርሶ በ239 ሄክታር መሬቱ ላይ የበቆሎ ዘር መዘራቱን አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ19 በላይ የተለያዩ የሰብል ዘሮችና 80 የሚጠጉ ዝርያዎችን በተለያዩ የዘር ደረጃዎች ማባዛቱ ተገልጿል።

በተጨማሪም የመነሻ ዘሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ዘር የማባዛትና የማሰራጨት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ማህበራዊ ጉዳዮች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለኢዜአ አስታውቀዋል።

ከአግሮ ኬሚካል አቅርቦት አኳያም ኮርፖሬሽኑ የፀረ-አረም፣ የፀረ-በሽታ፣ የፀረ-ተባይና የፀረ-መጋዘን ነፍሳት ተባዮች ኬሚካሎች እንዲሁም በሰው ኃይል የሚታዘሉ የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን ከውጭ በማስገባት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም