የመከላከያ የሠላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል የሚሰጠውን ሥልጠና ለማስፋት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ የሠላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል የሚሰጠውን ሥልጠና ለማስፋት እየሰራ ነው
ግንቦት 28/2013 (ኢዜአ) የመከላከያ የሠላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል የሠራዊቱን የመፈጸም አቅም ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ማህበር አባላት ዛሬ የመከላከያ የሠላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከልን ጎብኝተዋል።
የማዕከሉ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
አሁንም በተለያዩ አገራት ሠራዊት አባላቱን በመላክ ለዓለም በተለይም በአፍሪካ ሠላም ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኗን ነው የገለጹት።
ይህም ሆኖ በሠላም ማስከበር ሥራው የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልጸው ችግሮቹን ለማቃለል የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከአቅም ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በሥልጠና ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሚያካሂደውን ተቋማዊ የለውጥ ሥራ ተከትሎ ማዕከሉም ተልዕኮውን ለማሳካት የሪፎርም ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የአገሪቱን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን የዘርፉ ክፍተት ለመሙላት እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው፤ ሠራዊቱ ለዓለም ሠላምና ደህንነት እየሰራ ነው ብለዋል።
የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በጋራ ደህንነትና ትብብር ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ተልዕኮዎቹ ግብ እንዲመቱ ከሠላም ወዳድ አገራት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ በሠላም ማስከበር የምታደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ይህም ሆኖ በተለይም በአገር ውስጥ እየተካሄደ ካለው የሠላም ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ ሠራዊቱን የማጠልሸት ዘመቻዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትላንትም በመርህ ላይ ተመርኩዞ የተሰጠውን አገራዊ ተልዕኮ ሙያዊ ሥነ-ምግባሩን በተላበሰ መልኩ የሚወጣ ኃይል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ከዚህ በተቃራኒ የሚሰራጨው የሐሰት ዘገባ መሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ ሃቅ እንደማያሳይ ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ተናግረዋል።