ቀጥታ፡

"ኢዜማ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከሚጠበቁት ጋር በጋራ ይሰራል፤ የህልውና አደጋ የሚፈጥሩትን ይታገላል" --ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

ግንቦት 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከሚያስጠብቁ ኃይሎች ጋር እንደሚሰራና የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉትን ደግሞ እንደሚታገል የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ  እና ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት አማራጭ የፖለቲካ ሃሳቦችን በማምጣት ዴሞክራሲን መገንባት የሚቻለው በቅድሚ የአገር ህልውና ሲጠበቅ ነው።

በመሆኑም ኢዜማ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥሉ አካሄዶችን እንደሚቃወም አስረድተዋል።

ፓርቲያቸው የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ በሀገር ህልውና ላይ አደጋ ለማድረስ የሚጥሩትን ደግሞ ብጽኑ እንደሚታገል ተናግረዋል።

ኢዜማ ኢትዮጵያ ደህንነቷን እና ህልውናዋን ለማስጠበቅ ከሚጠቅሟት የጎረቤት አገራት ጋር በቅንጅት የመስራት መብት እንዳላት እንደሚገነዘብም ነው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ያብራሩት።

በማናቸውም ሁኔታ በኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተጽእኖ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት የሌለውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቴን ለማስጠበቅ ይጠቅሙኛል ያለቻቸውን አካሄዶች የመከተል መብት እንዳለትም አስገንዝበዋል።

ነገር ግን መንግስት በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላትን ለፍርድ የማቅረብ ግዴታ አለበት ነው ያሉት።

በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ዋነኛ ተጠያቂ ህወሓት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በዘር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፤ ሀይማኖትና ፖለቲካን በመደበላለቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩንና አካሄዱ አደገኛ በመሆኑ ከወዲሁ ሊታረም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የፖለቲካ አካሄዶች ከስሜት በጸዳ መልኩ በብልሃት መመራት እንዳለባቸውም ነው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም